ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራውያኑ ሴት ስደተኞች በኬንያ መጥፋታቸው ጭንቀት ውስጥ የከተታቸው ቤተሰቦች
ሁለት ኤርትራውያን ስደተኞች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ከስድስት ወራት በፊት መጥፋታቸውን ተከትሎ ቤተሰቦቻቸው የሁለቱ ሴቶች ዕጣ ፈንታ አለመታወቁ ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል።
ከጠፉት መካከል አንዷ የሆነችው ራሔል መርሐዊ አባት ለቢቢሲ ትግርኛ እንደገለፁት የልጃቸውን ድምፅ ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ የሰሙት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ነበር።
በወቅቱም ሰላማዊት አምባሰር ከተባለችው ጓደኛዋ ጋር ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ኬንያዋ የድንበር ከተማ ሞያሌ መግባቷን እና በመዲናዋ ናይሮቢም ለመገናኘት አቅደው ነበር።
"ስልክ ደውላ ሞያሌ እንዳለች አሳወቀችኝ" በማለት አባትየው እያለቀሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከዚያም ናይሮቢም ትደርሳለች ብዬ ስጠብቅ ደብዛዋ ጠፋ" ብለዋል።
አባትዬው የልጃቸውን መጥፋት ተከትሎም እጃቸውን አጣጥፈው አልተመለከቱም ወደ ሞያሌም ሄደው "በተራሮች እና በሸለቆች ውስጥ ፈለግኳት ነገር ግን ላገኛት አልቻልኩም" በማለት ያስረዳሉ።
የሰላማዊት ወንድም እንዲሁ ተመሳሳይ መከራን እየተቀበለ እንደሆነ ያስረዳል "እህቴን በስልክ ማግኘት ሳልችል ስቀር ወደ ናይሮቢ ታመጣታለች የተባለችውን ግለሰብ ደወልኩላት። እሷም አይ ትመጣለች ጠብቃት ብትለኝም ሳትመጣ ቀረች" ብሏል።
እህቱ ናይሮቢ ሳትመጣ ስትቀር መጨረሻ ላይ ወደነበረችበት ከተማ ሞያሌ ተጓዘ ነገር ግን ሊያገኛት አልቻለም።
ሁለቱ ኤርትራውያን በትግራይ ክልል በስደተኝነት ሲኖሩ የነበረ ሲሆን በጥቅምት ወር ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው ለስደት የተዳረጉት።
አንድ የኤርትራ የስደተኞች ቡድን በቅርቡም መጥፋታቸውን በተመለከተ እና ስደተኞች የሚገጥማቸውን መከራ በተመለከተም በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
በትግራይ ጦርነቱ ሲነሳ በአገራቸው የፖለቲካ ጭቆናና የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ሸሽተው የመጡ 100 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖሩ ነበር።
እንደ ራሔል እና ሰላማዊት በርካቶችም ህይወታቸውን ለማዳን እንደገና ለመሸሽ ተገደዋል።