የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች ያለው የሰዎች መፈናቀል አሳስቦኛል አለ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በአማራ እና አፋር ክልሎች ያለው የሰዎች መፈናቀል አሳስቦኛል አለ።

ይህ የተባለው የኮሚሽን ድርጅቱ ቃል አቀባይ ቦሪስ ቼሽርኮቭ በጀኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የአካባቢው ባለሥልጣናትን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ -ኦቻን ጠቅሶ ከአማራ ክልል 100 ሺህ እንዲሁም ከአፋር ክልል 70 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል።

የፌደራል መንግሥት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሓት አማጺያን በአማራ እና በአፋር ክልል ላይ ጥቃት ከፍተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከሁለቱ ክልሎች ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የአፋር ክልል የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ኻሎይታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልላቸው 76 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለው በአራት መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ።

የአማራ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው "በራያ በኩል ብቻ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ይህ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ተደምሮ በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች አሉ" ብለዋል።

ጦርነቱ በመቀጠሉም የተፈናቃዮች ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ትናንት ባወጣው "በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተላለፈ መልዕክትና አገራዊ ጥሪ!" በሚል ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የአገሪቱ ሠራዊትና የክልል ኃይሎች አማጺው ቡድንን "እንዲደመስሱ" አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል።

በሌላ በኩል የስደተኞች ድርጅቱ እና አጋር ድርጅቶቹ በትግራይ ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙባቸውን ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን መድረስ መቻላቸውን ገልጿል።

ድርጅቱ እንዳለው በአካባቢው የነበረው ጦርነት የድርጅቱ ሠራተኞች ከሐምሌ 7 በኋላ ወደ መጠለያ ጣቢያዎች እንዳይሄዱ አድርጓቸው ነበር።

ከሐምሌ 28 ቀን ጀምሮ ግን በሁለቱም መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 23 ሺህ ስደተኞች አስቸኳይ እርዳታ ማድረስ መጀመሩን ድርጅቱ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ባለው ውስብስብ የፀጥታ ችግር ምክንያት ስደተኞችን ለመድረስ ያለው እድል ውስን ነው ብሏል ድርጅቱ። በዚህም ምክንያት ስደተኞቹ አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

የስደተኛ ድርጅቱ በማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ ያሉ ስደተኞች ወደ ተዘጋጀላቸው አዲስ መጠለያ ጣቢያ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲዘዋወሩ ጥሪ አቅርቧል።

አለምዋች የሚገኘው አዲሱ መጠለያ ጣቢያ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ከዳባት ወረዳ በ135 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽኑ እና የኢትዮጵያ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጄንሲ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የመጀመሪያዎቹ 126 ስደተኞች ወደ ሥፍራው ተዛውረዋል ብሏል።

በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ ያለው ሁኔታ የተሻሻለ ነው ያለው ኮሚሽኑ፤ ባለፈው ሳምንት አስቸኳይ እርዳታ የያዙ 12 ተሽከርካሪዎች መቀለ መግባታቸውን አስታውሷል።

ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑንም ኮሚሽኑ አክሏል። ባለፈው ወር 40 ኤርትራውያን ስደተኞችን ጨምሮ ከ275 በላይ የሚሆኑት ስደተኞች በትግራይ ድንበር ከሚዋሰነው ሃምዳይት መጠለያ ጣቢያ መድረሳቸውንም ጠቅሷል።

ከአማራ ክልል 900 የሚሆኑ የቅማንት ማህበረሰብ አባላትም በጋላባት አድርገው ሱዳን መግባታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚገኙ 96 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞችን፣ ትግራይ ውስጥ የተፈናቀሉ 650 ሺህ ሰዎችን እንዲሁም በምስራቅ ሱዳን የሚገኙ 120 ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመርዳት 164.5 ሚሊየን ዶላር በአስቸኳይ ያስፈልጋል ብሏል።