በትግራይ የምግብ እጥረት እና የሕፃናት ጥቃት መባባሱ ተገለጸ

ዓለም አቀፍ ተቋማት በትግራይ ክልል በርካታ ነዋሪዎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ሕፃናት የጥቃት ሰለባ መሆናቸውቸውን ገለጹ።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የተመድ የህጻናት አድን ድርጅቱ ዩኒሴፍ ባወጡት መግለጫ ነው በክልሉ የምግብ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲደረግ እንዲሁም ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱን የጠቆሙት።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል 5.2 ሚሊዮን ሰዎች በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስታውቋል።

ከክልሉ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዋሪ በአፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንዲያገኝ 203 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውም ድርጅቱ አስታውቋል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፤ ከመጋቢት ጀምሮ የምግብ እርዳታ ባከፋፈለባቸው ሁለት የክልሉ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ረድቷል።

እነዚህ የምግብ እርዳታ ካገኙ ዜጎች ባሻገር አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ በአፋጣኝ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ግንቦት 24፣ 2013 ዓ. ም. የወጣው የድርጅቱ መግለጫ ይጠቁማል።

በያዝነው ሳምንት ሰኞ እለት ለ4,500 ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ መደረጉ ተገልጿል። እርዳታው የሚሰጠው በየስድስት ሳምንቱ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ 2.1 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ መታቀዱ ተጠቁሟል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለልጆች፣ ለነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች የአደጋ ጊዜ የምግብ እርዳታ እያደረገ ቢሆንም "በተለይም በገጠር አካባቢዎች ነዋሪዎችን በቀላሉ መድረስ አልተቻለም" ብሏል።

ድርጅቱ ለኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ለሚገኙ አጋሮቹ 40,000 ሜትሪክ ቶን ምግብ እንደሰጠ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ 20,000 ሜትሪክ ቶን ምግብ ለትግራይ ክልል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ቢሮ አስረክቧል።

ስለ ሕፃናት ጥቃት

በተባበሩት መንግሥታት ሥር የልጆችን ጉዳይ የሚከታተለው ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ "በትግራይ ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰት እየተባባሰ ነው" ብሏል።

ግንቦት 24፣ 2013 ዓ. ም. በወጣው መግለጫ የዩኒሴፍ ዋና ኃላፊ ሄንሬታ ፎር እንዳሉት፤ እስካሁን ድረስ ከ6,000 በላይ ከወላጆቻቸው የተለዩ ወይም ጠባቂ የሌላቸው ልጆች ተመዝግበዋል።

"በደኅንነት ስጋት ወይም የግጭቱ ተሳታፊዎች እገዳ ስላደረጉብን መድረስ ባልቻልንባቸው አካባቢዎች ከዚህ በላይ እርዳታ የሚሹ ልጆች አሉ ብለን እንሰጋለን" ብለዋል።

በክልሉ የቴሌኮምንኬሽን መቆራረጥ ስላለ እንዲሁም የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪዎች ውስን ስለሆኑ ልጆችን ከወላጆቻቸው ለማገናኘት ከባድ መሆኑን ዋና ኃላፊዋ አክለዋል።

በክልሉ ሴቶች አሁንም ድረስ "ለአሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃት ተጋልጠዋል" ብለዋል ሄርኔታ።

ዩኒሴፍ ከጥቅምት ጀምሮ 540 ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን መርዳት ቢችልም፤ በደኅንነት ስጋት እና ሴቶቹ በድጋሚ በበቀል የተነሳሳ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል በሚል ፍርሀት በርካቶች እርዳታ ሳያገኙ እንደቀሩ አስረድተዋል።

"ታዳጊ ወንዶች እንመለመላለን ብለው ይሰጋሉ" ሲሉም ተናግረዋል።

በህወሓት እና በመከላከያ ሠራዊቱ መካከል ጥቅምት ላይ የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ 1.6 ሚሊዮን ሰዎች እንደተፈናቀሉና ከእነዚህ መካከል 720,000 የሚሆኑት ታዳጊዎች እንደሆኑ የዩኒሴፍ መግለጫ ይጠቁማል።

ዋና ኃላፊዋ ሄርኔታ እንዳሉት፤ መጠለያ ካምፖች በሰው ከመጨናነቃቸው ባሻገር ንጽህናቸው ያልተጠበቀ፣ ደኅንነታቸውም የማያስተማምን ናቸው።

በተያያዘም "ከሚያዝያ ጀምሮ ዩኒሴፍ የሚደግፋቸው 31 የጤና፣ የምግብና ውሃ አቅራቢ ሚሽኖች እርዳታ እንዳያቀርቡ ታግደዋል። ለዚህም ምክንያቱ የደኅንነት ስጋት እና እርዳታ አቅራቢዎች ጥቃት ስለተሰነዘረባቸው ጭምር ነው" ብለዋል።

ዩኒሴፍ ሁሉም ወገን ለሕፃናት ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ዋና ኃላፊዋ በመግለጫው "ሁሉም ወገን ልጆችን ከጥቃት፣ ከብዝበዛ እና ከቤተሰብ ከመነጠል እንዲጠብቅ እንጠይቃለን" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።