ማክሮን የፈረንሳይ ጦርን ከማሊ ላስወጣ እችላለሁ ሲሉ አስጠነቀቁ

በማሊ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወደ ኢስላማዊ አክራሪነት አገሪቱን የሚመራት ከሆነ ፈረንሳይ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን አስጠነቀቁ።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ አይዘነጋም።

ፕሬዝዳንት ማክሮን ማሊ ከፍተኛ ወደሆነ ኢስላማዊ ተጽህኖ እየተጠጋች ነው ብለዋል።

ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ሳህል አካባቢ 5ሺ 100 ወታደሮችን ያሰፈረች ሲሆን ለበርካታ ዓመታት ኢስላማዊ ታጣቂዎችን ስትዋጋ ቆይታለች።

የፈረንሳይ ወታደሮች ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ ለማሊ፣ ሞሪታንያ፣ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና ቻድ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንቱ 'ሌ ዦርናል ደ ዲማንሽ' ከተባለው ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ሁኔታ የመንግሥት ለውጥ የሚያደርጉ አገራትን መደገፍ እንደማይፈልጉና ወታደሮቿንም በአፍሪካ ለዘላለም የማቆየት ሀሳብ እንደሌላቸው ለአካባቢው አገራት መሪዎች መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ላለፉት አስርት ዓመታት ፈረንሳይ በቀድሞ የቅኝ ግዛቷ ስር ለነበሩ አገራት መሪዎች ወታደራዊ ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ወታደሮችን በመላክና አማጺያን ላይ የአየር ድብደባ በማድረግ ትሳተፋለች።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ችግር በማያጣው የሳህል አካባቢ የሚገኙ ወታደሮችን ቁጥር ስለመቀነስ አልያም ከነጭራሹ ስለማስወጣት ማውራት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።

በርካታ ኢስላማዊ ታጣቂዎችና አማጺያን በማይጠፉበት ይህ የሳህል አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር ሌሎች የአውሮፓ አገራት ቁርጠኝነት አለማሳየተቸውንም ማክሮን ተችተዋልቱ።

ኢስላማዊ ታጣቂዎቹ ለአውሮፓ ስጋት እንደሆኑ ነው የሚታሰበው። የመጀመሪያው አክራሪዎች የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሕገ-ወጥ የስደተኞች ዝውውር ጋር የተያያዘ ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበሩት ማሊና ቻድ ያለው አለመረጋጋት ፕሬዝደንት ማክሮንን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ማሊ ውስጥ ሁለት የመፈንቅለ መንግሥት የተካሄደ ሲሆን በቻድ ደግሞ አንድ መፈንቅል መንግሥት ተደርጓል።

ፕሬዝዳንቱም በሁለቱ አገራት ያለው ወታደራዊ አገዛዝ እንዲቆም ሲጠይቁ ነበር። ማሊ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ አገሪቱን ወደ አክራሪ ኢስላማዊ አስተዳደር የሚመራት ከሆነ ወታደሮቻቸውን እንደሚያስወጡም ዝተዋል።

ነገር ግን ሁኔታው እንዲህ በቀላሉ የሚወጡት አልሆነላቸውም።

የፈረንሳይ ጦር ከአከባቢው ጠቅልሎ የሚወጣ አክራሪ ኢስላማዊ ቡድኖች በስፋት መንቀሳቀስ እንዳይጀምሩ ስጋት ፈጥሯል።

በማሊ የተፈጠረው ምንድነው?

ከትናንት በስቲያ የማሊ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታን የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰይሟል።

ኮሎኔል ጎይታ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለተኛውን መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ከያዙ ከሁለት ቀናት በኋላ ባለፈው ረቡዕ የማሊ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝደንት አድርገው እራሳቸውን ሾመዋል።

በምርጫ ሥልጣን ይዘው የነበሩትን ፕሬዝዳንት ቡባካር ኬይታን ከመንበራቸው ባለፈው ነሐሴ ወር ያስወገዱት ወታደራዊ መሪው፤ የፕሬዝደንትነት ቦታውን እንዲይዙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ከመጀመሪያው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ማሊን ወደ ሲቪል መንግሥት የሚመልሰውን አስተዳደር በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የነበሩት ባህ ዳዋ እና ሞክታር ኦኔ በሁለተኛው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ተይዘው ታስረዋል።

ኮሎኔል ጎይታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል እንዲታሰሩ አድርገዋል። ነገር ግን ሁለቱ መሪዎች ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ ሐሙስ ዕለት ከእስር ተለቀዋል።

የባለፈው ዓመት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሽግግሩ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

መፈንቅለ መንግሥቱ የተካሄደው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአገሪቱ ጦር ሠራዊትን ሁለት ከፍተኛ መኮንኖችን ከሥልጣናቸው በማንሳት በሌላ ከተተኩ ከሰዓታት በኋላ ነበር።

ይህን ተከትሎ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሹም ሽር በማድረጉ ኮሎኔል ጎይታ ቅሬታ አድሮበት ነው እርምጃውን የወሰደው ተብሏል።