ትራምፕ ዳግም ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2024 እንደገና ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ።
ትራምፕ ፍሎሪዳ በተካሄደ የወግ አጥባቂ የሪፐብሊካን ኮንፈረንስ ላይ የሪፓብሊካኖችን ድምጽ ሊከፋፍል ይችላል በሚል አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው፤ የአሜሪካ ፖሊሲ "ከቅድሚያ ለአሜሪካ ወደ አሜሪካ መጨረሻ" ተቀይሯል ብለዋል ተተኪያቸውን አጥብቀው በተቹበት ንግግራቸው።
ትራምፕ ትናንት በተካሄደው በኮንሰርቫቲቭ ፖሊቲካል አክሽን ኮንፈረንስ (ሲፒኤሲ) ላይ መገኘታቸው በሪፐብሊካን ፓርቲ ላይ አሁንም ያላቸውን ተጽዕኖ ያሳያል ተብሏል።
ሐሙስ በተጀመረው ጉባኤ ለትራምፕ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን የቴክሳሱ ሴናተር ቴድ ክሩዝን እና የትራምፕ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየርን ጨምሮ ሌሎችም ደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባለፈው ጥር በአሜሪካ ካፒቶል ለደረሰው አስከፊ አመፅ በሰጡት ምላሽ ፌስቡክ እና ትዊተርን ጨምሮ ከማህበራዊ ድር አምባዎች ታግደዋል።
ትራምፕ ከኋይት ኃውስ ከወጡ በኋላም በማር-ላ ላጎ ፍሎሪዳ የጎልፍ ሪዞርት እኖሩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዶናልድ ትራምፕ ምን አሉ?
የ74 ዓመቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ህያት ሬጀንሲ ሆቴል ከአንድ ሰዓት በላይ ዘግይተው ሲደርሱ ደጋፊዎቻቸው ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል። አብዛኛው ታዳሚ የአፍና የአፍንጫ ጭምብል አላደረጉም ነበር።
"ከአራት ዓመት በፊት አብረን የጀመርነው አስገራሚ ጉዞ ገና ያላለቀ መሆኑን ለማሳወቅ ዛሬ ከፊታችህ ቆሜያለሁ" ብለዋል ትራምፕ።
ስለ ወደፊቱ ለመነጋገር ዛሬ ተሰብስበናል - ስለ እንቅስቃሴያችን፣ ስለፓርቲያችን እና ስለሃገራችን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመነጋገር።
አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ሊመሠርቱ ይችላል የሚለውን ሀሳብ ውድቅ አደርገው መረጃዎቹን "የሐሰት ዜና" በማለት ገልጸዋል።
"ይህ ድንቅ አይደለም? አዲስ ፓርቲ መሥርተን ድምፃችንን ከፋፍለን በጭራሽ እንዳናሸንፍ" ሲሉ ጠይቀዋል።
"ሪፐብሊካን ፓርቲ አለን። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድ እና ጠንካራ እየሆነ ነው" ብለዋል።
በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከመሸነፍ ባለፈ በጥሩ አመጽ ከፍተኛ ወቀሳ ቢሰነዘርባቸውም ትራምፕ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ አሁንም ድረስ በጣም ተወዳጅ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት 46 በመቶ የሚሆኑት የትራምፕ መራጮች ሪፐብሊካኖቹን ትተው የራሳቸውን ፓርቲ ቢመሠርቱ እንደሚመርጧቸው ጠቁሟል።
ትራምፕ በንግግራቸው በዲሞክራቶች የተሸነፉት ምርጫው በመጭበርበሩ መሆኑን ገልጸዋል። በ2024 ስለመወዳደራቸው ፍንጭ ሲሰጡም "ግን ማን ያውቃል? ለሦስተኛ ጊዜ እንኳን እነሱን ለማሸነፍ እወስን ይሆናል" ብለዋል።
ትራምፕ የኢሚግሬሽን እና በድንበር ደህንነት ላይ ያላቸውን አቋም በመለወጡ ባይደንንና አዲሱን አስተዳደራቸውን ተችተዋል።
"የባይደን አስተዳደር መጥፎ እንደሚሆን ሁላችንም እናውቅ ነበር። ማናችንም ብንሆን ግን ምን ያህል መጥፎ እንደሚሆኑ እና እስከ ምን ያህል ግራ ዘመም እንደሚሆኑ አላሰብንም" ሲሉ በደስታው ድጋፉን ሲሰጣቸው ለነበረው ህዝብ ተናግረዋል።
በጎርጎሮሳዊያኑ 1974 የተጀመረው ኮንፈረንስ፤ የአሜሪካ ወግ አጥባቂዎች የሚሰባሰቡበት ሲሆን የሪፐብሊካን ፓርቲ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚለካበት ተደርጎ ይወሰዳል።












