ትግራይ፡ ለህይወታችን እንሰጋለን ያሉት የኢትዮጵያ የተመድ ሰላም አስከባሪዎች

169 የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የዛሬ ሳምንት ሰኞ ወደ አዲስ አበባ ይመለሱ ነበር ተብሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ሳምንት ሰኞ በደቡብ ሱዳን ተሰማርተው የነበሩት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ለመብረር በተዘጋጀ አውሮፕላን አንሳፈርም ብለው ነበር።

የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ብንመለስ እስር እና ክስ ይገጥመናል በሚል ይሰጋሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አባይ "የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት በጁባ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኢትዮጵያ ወታደሮች ታስረው አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።

ባሳለፍነው ማክሰኞ የአገር መከላከያ ሚንስትር ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ሞሐመድ ተሰማ በሰላም አስከባሪ ኃይል አባላቱ ላይ ደረሰ ስለተባለው እስር እና አካላዊ ጥቃት ያሉት ነገር ባይኖርም፤ በቁጥር 15 የሆኑት ወታደሮች "በጁባ አየር ማረፊያ መሬት እየተንከባለሉ እና እየጮሁ ሁከት ፈጥረው ነበር" ሲሉ ከስሰዋል።

በአሁኑ ወቅት 15 የሰላም አስከባሪ ኃይሉ አባላት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና በደቡብ ሱዳን መንግሥት ጥበቃ ስር ይገኛሉ።

ከ15ቱ ወታደሮች አንዱ የሆነው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ኮሎኔል ለቢቢሲ እንደተናገረው ባሳለፍነው ሕዳር ወር በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ፤ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ወታደሮች ኢላማ እንደሚደረጉ እና መገለል እንደሚደርስባቸው ተናግሯል።

ይህ ኮሎኔል እንደሚለው ከሆነ ጥገኝነት እየጠየቁ የሚገኙት የትግራይን ጦርነት በመቃወማቸው፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ እንዲወጡ እና በክልሉ የምግብ እጥረት መኖሩ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

"የትግራይ ቀውስን ተከትሎ ኢላማ ውስጥ ገብተን ነበር፤ በጦሩ ውስጥ ያሉ ባልደረቦቻችንም መታሰራቸውን አውቀናል። እና ምንም በማይመለከተን ጉዳይ ነው መንግሥት የሚከስሰን። ከዚህ የሰላም ማስከበር ዘመቻ በኋላ የተመለሱ በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው ይገኛሉ። ይህ ሁሉ ነገር ነው እንድንሰጋ ያደረገን" በማለት ይህ ኮሎኔል ይናገራል።

"ትጥቅ አስፈቱን፣ ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምር ሰዓት እላፊ አወጁ እንዲሁም የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ባልደረቦቻችን በአይነ ቁራኛ ይመለከቱናል"

በተባበሩት መንግሥታት ጥበቃ ሥር ያለ ሌላ ሳጅን በትግራይ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እንቅስቃሴያቸው በክትትል ሥር እንደነበረ ይናገራል።

"በማንነታችን እንደጠላት ታይተናል ማለት እችላለሁ። እንቅስቃሴያችን ተገድቦ ለወራት በክትትል ሥር ቆይተናል። ከሌሎች እንድንለይ ተደርገን ከሌሎች ወታደሮች ጋር እንዳንገናኝ ተደርገናል። ከኢትዮጵያ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን ውጪ ሌሎች መገናኛ ብዙሃንን እንድንመለከት አይፈቀድም። ሙሉ በሙሉ ነጻነታችን ተገፈን ነበር" በማለት ይከስሳል።

line

በትግራይ ክልል ግጭቱ የተቀሰቀሰው ሕወሓት በክልሉ የሚገኘውን የፌዴራል ጦር ሠፈር በማጥቃቱ ነው። ይህ የሕወሓት እርምጃ የፌዴራል መንግሥቱ የአፀፋ ምላሽ እንዲሰጥ አድርጎታል።

በፌዴራል መንግሥቱ በክልላዊው አስተዳደር መካከል ያለው ውጥረት የጦዘው የኢትዮጵያ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት መራዘሙን ተከትሎ ነው።

ከቀናት በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ 15 የትግራይ ተወላጅ ሰላም አስከባሪዎች አሁን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ጥላ ሥር ይገኛሉ ብለዋል።

"ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ማንኛውም ሰው ከለላ ሲፈልግ ጥገኝነት የመጠየቅ መብት አለው። ዓለም አቀፍ ከለላ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ከታመነበት ማንኛውም ሰው ነፃነቱን አሊያም ሕይወቱን ወደሚያጣበት ሃገር መመለስ የለበትም። ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልነው ነው።"

ጥገኝነት የጠየቁ ግለሰቦች አሁን ደህንነታቸው በተጠበቀ ቦታ እንዳሉ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደቡብ ሱዳን ያሉ 15 የሰላም አስከባሪ አባላቱ ወደ ሃገር ቤት ላለመለስ መወሰናቸውን አረጋግጧል።

ሰላም አስከባሪዎቹ በተባበሩት መንግሥታ የደቡብ ሱዳን ሚሽን መሠረት በሌሎች አዳዲስ ወታደሮች መተካት ነበረባቸው።

ባለፈው ማክሰኞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሞሐመድ ተሰማ 15ቱን ወታደሮች "የሃገራቸውንና የወታደሮችን ስም ያጠፉ ናቸው" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

"ጁባ አየር ማረፊያ እየጮሁና መሬት ላይ እየተኙ ግርግር ሲፈጥሩ ነበር" ብለዋል ሜጀር ጄኔራሉ።

ጄኔራሉ አክለው ለወታደሮቹ ከለላ የሰጠው የተመድ ስደተኞች ተቋምን [ዩኤንኤችሲአር] "የተዛባ መረጃ አሰራጭቷል" ሲሉ ወቅሰዋል።

እንደ ኮሎኔሉ ከሆነ ከ200 በላይ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ወታደሮች ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሰላም ማስከበር ተሰማርተው ከ18 ወራት በላይ አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ እንደሚሉት 15 ወታደሮች ከኢትዮጵያ ከመጡ 169 የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ሚሽን አባላት መካከል ናቸው። ወታደሮቹ በሚሽኑ መሠረት በሌሎች ወታደሮች ሊተኩ ነበር።

ቃል አቀባዩ አክለው በሚሽኑ ውስጥ ካሉ 17 ሺህ 200 ወታደሮች መካከል 2 ሺህ 100 ኢትዮጵያዊያን ወታደሮችና ሲቪሎች ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የአስራ አምስቱን ጥገኝነት የተቀበለ ሲሆን ሌሎች አራት "በደረሰብን ጥቃት" ጉዳት ገጥሞናል ያሉ ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ እርዳታ እያገኙ ይገኛሉ።