የአውሮፓዋ አዛውንት በ117ኛ ልደታቸው ዋዜማ ከኮቪድ-19 አገገሙ

በአውሮፓ በእድሜ ትልቋ የሆኑት መነኩሴ 117ኛ ዓመት ልደታቸውን ከማክበራቸው በፊት ከኮሮናቫይረስ አገገሙ።

ሊሲሊ ራንደን የተባሉት መነኩሴ ቫይረሱ የተገኘባቸው ጥር 16 ሲሆን፤ የበሽታው ምልክት አልታየባቸውም ነበር።

"በሽታው እንደያዘኝ አላወቅኩም ነበር" ብለዋል አዛውንቷ።

በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኘው ቶውሎን የተባለው ግዛት በአረጋውያን መጦሪያ ቤት እየኖሩ ያሉት መነኩሴዋ አሁን ከበሽታው ሙሉ በሙሉ አገግመዋል።

መነኩሴዋ አይነ ስውር ናቸው። የሚንቀሳቀሱትም በዊልቸር ነው። 117ኛ ልደታቸውን ለማክበርም እየጠበቁ ነው።

በልደት በዓላቸው ላይ በጡረተኞች መኖሪያው ያሉ ጥቂት ሰዎች ይገኛሉ ተብሏል።

የአረጋውያን መጦሪያው ቃል አቀባይ ዴቪድ ታቬላ "በጣም እድለኛ ናቸው" ሲል ስለ እድሜ ባለጸጋዋ ተናግሯል።

ቫይረሱ እንዳለባቸው ሲነገራቸው "ምግብ የምበላበትና የምተኛበትን ሰዓት መቀየር ይጠበቅብኛል" ብለው እንደጠየቁት ያስታውሳል።

ከዚያ ባለፈ ግን በሽታው ሊጎዳኝ ይችላል የሚል ጭንቀት አልተሰማቸውም።

"ህመሙን አላስፈራቸውም ነበር። እንዲያውም ያስቡ የነበረው እዚ ለሚኖሩ ሌሎች አረጋውያን ነበር" ይላል ቃል አቀባዩ።

እአአ በ1904 የተወለዱት በአውሮፓ በእድሜ ትልቋ ሰው ይባላሉ። በዓለም የዘረ መል ምርምር ጣቢያ መረጃ መሠረት በዓለም ሁለተኛዋ የእድሜ ባለ ጸጋ ናቸው።

በቫይረሱ መያዝ አስፈርቶዎት ነበር? ብሎ የፈረንሳዩ ቢኤፍኤም ሲጠይቃቸው "መሞት ስለማያስፈራኝ በቫይረሱ መያዝ አላስፈራኝም። ከእናንተ ጋር መሆኔ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ከሞት በኋላ ከታላቅ ወንድሜና ከአያቶቼ ጋር ብቀላቀል የበለጠ ደስ ይለኛል" ብለው መልሰዋል።