ኮሮናቫይረስ ፡ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቲቪ እየታዩ ተከተቡ

የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ሆነው የተመረጡት ጆ ባይደን በቴሌቭዥን እየታዩ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ተከተቡ።

ባይደን የመጀመሪያውን የክትባት ጠብታ ሲወስዱ፤ አሜሪካውን ክትባቱን መውሰድ "አስተማማኝ መሆኑን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የፕሬዘዳንት ትራምፕ ምክትል የሆኑት ማይክ ፔንስ፣ አፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ እና ሌሎችም የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በቴሌቪዥን እየታዩ ተከትበዋል።

ሞደርና ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ውስጥ ፍቃድ ከተሰጠው ወዲህ ክትባቱ መሰጠት ተጀምሯል። ከ500 ሺህ በላይ አሜሪካውያን መከተባቸውም ተገልጿል።

ባይደን ሲከተቡ "ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ማሳሳብ እፈልጋለሁ። ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም" ብለዋል።

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ክትባት በማስጀመሩ እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የባይደን ባለቤት ጂል የመጀመሪያ የክትባት ጠብታ ወስደዋል።

የባይደን ምክትል ሆነው የተመረጡት ካምላ ሀሪስ እና ባለቤታቸውም በመጪው ሳምንት ክትባት ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባይደን ዋይት ሀውስ ከገቡ በኋላ ባሉት 100 ቀናት ውስጥ 100 ሚሊዮን ክትባት የመስጠት እቅድ አላቸው።

አሜሪካ ውስጥ ከ18 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 319 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል።

ቫይረሱ ይዟቸው 3 ቀን ሆስፒታል ያሳለፉት ትራምፕ ክትባቱን ስለመውሰዳቸው ያሉት ነገር የለም።

ሆኖም ግን "ክትባቱን ለመውሰድ መርሀ ግብር አልያዝኩም። በትክክለኛው ጊዜ ክትባቱን ለመውሰድ ግን እጠባበቃለሁ" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።

ክትባቱ መጀመሪያ ለማን ይሰጣል?

ፋይዘር 3 ሚሊዮን ጠብታ አሜሪካ ልኳል። 6 ሚሊዮን የሞደርና ክትባትም ወደ አሜሪካ ለመግባት ዝግጅቱ ተጠናቋል።

በአሜሪካ በሦስት ደረጃ ክትባቱ ለእነማን እንደሚሰጥ መረጃ ወጥቷል።

ደረጃ 1ሀ- ክትባቱ ለ21 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎች ይሰጣል። በተጨማሪም 3 ሚሊዮን አረጋውያን ክትባቱን ያገኛሉ።

ደረጃ 1ለ- ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ አሜሪካውያን ይከተባሉ። ፖስታ አድራሾች፣ መምህራን፣ ነጋዴዎችን ጨምሮ 30 ሚሊዮን እጅግ አስፈላጊ አገልግሎት ሰጪዎችም ይከተባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ደረጃ 1ሐ- ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች ክትባቱ ይሰጣቸዋል። እነዚህ ለኮቪድ-19 የሚያጋልጥ ቀደም ያለ ህመም ያለባቸው 129 ሚሊዮን ሰዎች ናቸው።