ኮሮናቫይረስ ፡ በዩናይትድ ኪንግደም የኮቪድ-19 ተስፋ ሰጪ የክትባት ሙከራ ተጀመረ

ውጤታማ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሰዎችን ከኮቪድ-19 የሚከላከል የክትባት ሙከራ በዩናይትድ ኪንግደም ተጀመረ።

መሰል ሙከራዎች ሲካሄዱ ይህ ሦስተኛው ነው።

ክትባቱ የተዘጋጀው በአንድ የቤልጂየም ተቋም ሲሆን፤ የተሠራው ዘረ መሉ ከተሻሻለ የጉንፋን ቫይረስ ነው። ክትባቱ በሽታን የመከላከል አቅምን እንደሚያዳብርም ተነግሯል።

ከሳምንት በፊት ከበሽታው 90 በመቶ የሚከላከል ክትባት መገኘቱ ተሰምቷል።

ፋይዘር እና ባዮኤንቴክ የተባሉት ተቋሞች ያስተዋወቁት ክትባት ለዓለም ሕዝብ ተስፋን ሰጥቷል።

ሆኖም ግን ወረርሽኙን ለመግታት በርካታ የተለያዩ ክትባቶች ያስፈልጋሉ።

ፋይዘር እና ባዩኤንቴክ ያገኙት ክትባት ገና ፍቃድ አልተሰጠውም። በሽታው የመከላከል አቅሙ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ እና አረጋውያን ላይ ያለው ውጤታማነት እስካሁን አልታወቀም።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚካሄደውን ሙከራ የሚመሩት ፕሮፌሰር ሳውል ፋውስት "ከተለያዩ አምራቾች የተለያዩ ክትባቶችን መሞከር አለብን" ብለዋል።

እያንዳንዱ ክትባት ምን አይነት ውጤት እንደሚያሳይ እንደማይታወቅና በአንድ ድርጅት የሚመረት ክትባት ብቻ ለሁም ተደራሽ እንደማይሆን ተናግረዋል።

ከዩናይትድ ኪንግደም 6000 ሰዎች በሙከራው ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከሌሎች የተለያዩ አገራትም አስከ 30,000 የሚደርሱ ሰዎች ተሳታፊ እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

ከሙከራው ተሳታፊዎች ግማሹ በሁለት ወር ልዩነት ሁለት ጊዜ ክትባቱባቱን ያገኛሉ ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በአንድ ጠብታ ሙከራ ተሠርቷል።

ሁለት ጠብታ በመስጠት የክትባቱ በሽታ የመከላለከል አቅም ምን ያህል እንደሆነ ይፈተሻል።

ውጤቱ ሊታወቅ የሚችለው በስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ ክትባት ከፋይዘር ክትባት በተለየ መልኩ የጉንፋን ቫይረስን በማሻሻል የተሠራ ሲሆን፤ ጉዳት እንዳያስከትል እና ኮሮናቫይረስን እንዲመስል ተደርጎ ነው የተቀመመው።

ይህም ሰውነት ቫይረሱን እንዲያውቀውና እንዲዋጋው ይረዳል።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እና አስትራዜንካ የሚሠሩት ክትባትም ተመሳሳይ መንገድ ይከተላል።

በሌላ በኩል ይህኛው ክትባት የሚሞከረው በሰው ላይ ሲሆን፤ የኦክስፎርዱ ግን ዝንጀሮዎች ላይ ሙከራ እየተሠራበት ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 25 ሺህ ዜጎች በተለያዩ የክትባት ሙከራዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአገሪቱ መንግሥት እስካሁን ስድስት ክትባቶችን ለመግዛት ተስማምቷል። ከእነዚህ መካከል አዲሱን ክትባት 30 ሚሊዮን ጠብታ እንደሚገዛ አስታውቋል።