የአማራ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የተጠራው ሠልፍ ዕውቅና የለውም አለ

የአማራ ክልላዊ መንግሥት የፊታችን ረቡዕ በክልሉ ከተሞች የተጠራው ሠላማዊ ሠልፍ ዕውቅና የለውም ሲል አስታወቀ።

ይህን ያስታወቁት የአማራ የክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ናቸው። አቶ ግዛቸው በማህበራዊ ሚዲያ የተጠራው ሠልፍ ክልሉ እንዲረጋጋ ለማይፈልጉ ኃይሎች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚመች ነው ብለዋል።

የአማራ ክልልንም ሆነ ህዝቡን መሠረት በማድረግ በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ግጭት በመፍጠር አገር ለማተራመስ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች አሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) "በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ዘር ማጥፋት የሚያወግዝ " የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል።

አብን ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች ጥቅምት 22 ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ ለማካሄድ ነው በፌስቡክ ገጹ ላይ ጥሪ ያስተላለፈው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ እነዚህ ጸረ ለውጥ ሃይሎች የብሔር፣ የሃይማኖት እና የኢኮኖሚ አጀንዳ በመፍጠር አማራ በደል እንዲደርስበት እና ዝቅ እንዲል መሥራት ከጀመሩ ሰነባብወተዋል።

ይህ ዓላማቸው በክልሉ ውስጥ አልሳካ ሲላቸው በቅርቡ በቤኒሻንጉል አሁን ደግሞ በጉራ ፈርዳ ወረዳ ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ እየገደሉ ነው ብለዋል።

ክልሉ ግድያውን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ክልሎች ጋር በመሆን አጥፊዎች በህግ እንዲቀጡ እና ህግ እንዲከበር እየሠሩ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በርካታዎችም ለህግ የቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተጠራው ልፍ ዕውቅና የለውም ያሉት አቶ ግዛቸው "ችግሩን ሰልፍ በማድረግ ብቻ አይፈታም። ሰልፍ መፍትሔ ቢሆን የክልሉ መንግሥትም ገዢውን ፓርቲ በማስተባበር ሰልፍ በጠራ ነበር" ብለዋል።

ጸጉረ ልውጦች ሰልፉን በመጠቀም ግርግር ለመፍጠር እረየሰሩ መሆኑ ስለሚታወቅ መንግሥት ዕቀውቅና አይሰጠውም ብለዋል።

"በግምት አይደለም የምንነጋገረው። በተጨባጭ እዚህ ከልል ላይ ሰልፍ ቢካሄድ አሁን ባለው ሁኔታ ግጭቶች ይከሰታሉ። የተዘጋጁ የሚፈነዱ ቦምቦች አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ በተጠራው ሰልፍ ላይ እንዳይሳተፍ፤ አስተባባሪዎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰልፍ በሚወጡም ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

አቶ ግዛቸው መግለጫ እስከተሰጠበት ሰዓት ድረስ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ አለመቅረቡንም ጨምረው ተናግረዋል።