ነገ በሚቀጥለው ድርድር የትራምፕ አስተያየት አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖረውም ተባለ

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ተቋርጦ የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ከነገ ጀምሮ ቀጥሎ እንደሚካሄድ አስታወቁ።

ለሰባት ሳምንታት ተቋርጦ የነበረው ድርድር ከነገ ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምር ይፋ የተደረገው በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ ትዊተር ገጽ ላይ ነው።

ፕሬዝደንት ራማፎሳ ከሶስቱ አገራት መሪዎች ጋር ማለትም ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱ ፋታህ አል-ሲሲ፣ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ጥልቅ ምክክር ከተካሄደ በኋላ የሶስትዮሽ ድርድሩ ነገ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

ይህ ድርድር የሚቀጥለው ፕሬዝደንት ትራምፕ የሕዳሴ ግድብን ግብጽ "ልታፈነዳው ትችላለች" የሚል አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው አርብ ምሽት በዋይት ሃውስ ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት፤ ኢትዮጵያ ወደ ስምምነቱ መመለስ አለባት፤ ግብጽ ብትበሳጭ ልትኮነን አይገባም፤ "ያን ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች" ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ፤ የፕሬዝደንት ትራምፕን አስተያየት በተመለከተ በግድቡ ዙሪያ የሚሰጡ ማስፈራሪያዎች ከመረጃ ክፍተት የሚነሱ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ ናቸው ማለቷ ይታወሳል።

የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ነገ ቀጥሎ በሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ላይ አሉታዊ ጫና አያሳድርም ብለዋል።

"ድርድሩ ራሱን የቻለ ነው፤ ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት እየተደራደሩ ያሉበት ጉዳይ ነው። ፕሬዚደንቱን አይመለከትም። የሚመለከታቸው ነገር ካለ እንድንስማማ መገፋፋት፣ መደገፍ፣ እኛ የተስማማንበትን ነገር መቀበል ብቻ ነው እንጂ ከዚህ ውጭ ይሄ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ እየተደረገ ያለ ጉዳይ ስለሆነ የሌላ የማንም ሰው ጉዳይ ሊሆን አይችልም" ብለዋል አምባሳደር ዲና።

ፕሬዝደንት ራማፎሳ ሶስቱ አገራት ወደ ትብብር እና በቅን መንፈስ ተቀባይነት ወዳለው ድርድር ለመመለስ መወሰናቸውን በበጎ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሶስቱ አገራት በሕግ እና ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንደሚደርሱ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በአሜሪካ ዋሽንግትን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትካፈል ማስታወቋ ይታወሳል።

የካቲት 2012 ዓ. ም. ላይ ኢትዮጵያ በዋሽንግተን የመጨረሻ ቀጠሮ ተይዞለት በነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጣይ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ ለአሜሪካ አስታውቃ ነበር።

በአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት በአዲስ አበባ፣ ካይሮ፣ ካርቱም እና ዋሽንግተን ዲሲ ሲደረጉ የነበሩት ውይይቶች ያለ ውጤት እንዲበተኑ የሆነው የግብጽ መከራከሪያ ነጥቦች መለዋወጥ መሆኑ ተጠቁሟል።

ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች እንደተረዳው ምንም እንኳን የሚካሄደው ውይይት በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጥረት እያደረገች ቢሆንም ግብጽ ድርድሩ የውሃ ድርሻ ላይ እንዲያተኩር ግፊት እያደረገች ነው።