ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የፊት መከለያ መሳሪያ ያመረቱት የሥነ ሕንጻ ባለሙያ
አቶ አሸናፊ ዘመቻ በሙያቸው የሥነ ሕንጻ ባለሙያ ናቸው። ለሥራቸው የሚያግዟቸውን የተለያዩ ነገሮችም ዲዛይን በማድረግ ይሰራሉ።
ለዚሁ ስራቸውም እንዲረዳቸው በሚል የ3ዲ ፕሪንተር ያላቸው ሲሆን በዚያም የተለያዩ ባሕላዊ የሆኑ እቃዎችን፣ መብራቶችን ለማተም ይገለገሉበታል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ በቅርበት ጉዳዩን ሲከታተሉ እንደነበር የሚገልፁት አቶ አሸናፊ፣ በወቅቱ ወረርሽኙ ስጋት ውስጥ ከትቷቸው እነደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ከመደናገጥ ይልቅ ምን ዓይነት አስተዋፅኦ ላበርክት የሚል ሃሳብ ይዘው ዙሪያቸውን ሲቃኙ ባላቸው 3ዲ ፕሪንተር የተወሰነ አገለግሎት መስጠት እንደሚችሉ አሰቡ።
ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይና አልፎ አውሮፓ፣ አሜሪካ እንዲሁም አፍሪካን ሲያዳርስ ግለሰቦችንም ሆነ የሕክምና ባለሙያዎችን ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ለማድረግ በሙያቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያስቡም ባላቸው ሕትመት መሳሪያ የፊት መሸፈኛ መስራት እንደሚችሉም ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
ቻይና ላይ ቫይረሱ መከሰቱ በተሰማበት ወቅት ጀምሮ ጉዳዩ ያሳስባቸው እንደነበር ለቢቢሲ የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፣ በወቅቱበአገር ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ዋጋ በፍጥነት መናሩ እንዲሁም የአቅርቦት ችግር መኖሩ ማስተዋላቸው ምን ማድረግ አለብኝ ወደሚል ጥያቄ እንደመራቸው ይገልጻሉ።
3ዲ ፕሪንተር ካላቸው እና በእንግሊዝ አገር ከሚገኙ ሌሎች ባለሙያዎች ጋር በኢንተርኔት ላይ በነጻ የሚገኙ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ለአገራቸው የሚጠቅም ነገር ለማበርከትም አቀዱ።
በዚህ የፊት መሸፈኛ የሕክምና ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ፊታቸውን የሚከልሉበትን መሳሪያ ከበይነ መረብ ላይ በመመልከት ሰሩ።
እርሳቸው በ3ዲ ፕሪንተር ተጠቅመው ያመረቷቸውን የፊት መከለያዎች፣ ለሆስፒታሎችና ለሕክምና ባለሙያዎች በነጻ ሲሰጡ የፊት መከለያ መጠቀም በስፋት በባለሙያዎች ዘንድ አለመለመዱን ያስታውሳሉ።
መጀመሪያ ላይ ያመረቷቸውን የፊት መከለያዎች በነጻ ለተወሰኑ ሆስፒታሎችና የሕክምና ባለሙያዎች ለግሰዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም በግል ለሚያውቋቸው ሕክምና ባለሙያዎች በነጻም በሽያጭም መስጠት የጀመሩት አቶ አሸናፊ፣ ይህ የሕክምና ባለሙያዎች ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚከልሉበትን (ፌስ ሺልድ) መሳሪያ በበርካታ ባለሙያዎች ዘንድ ፍላጎትን በመፍጠሩ በክፍያ ለማቅረብ ተነጋገሩ።
ይህንን የፊት መከለያ ማንም የ3ዲ ፕሪንተር ያለው ግለሰብ በቀላሉ በሚጫኑ ሶፍት ዌሮችን በመጠቀም ማተም የሚችል ቢሆንም ህትመቱ ግን ዘገምተኛ በመሆኑ በብዛት ለማዳረስ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።
በአገር ውስጥ 3ዲ ፕሪንተር ያለው ግለሰብ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የገለፄት አቶ አሸናፊ ዘመቻ፣ ለህትመት የሚያገለግለው ቁስ በቀላሉ አለመገኘቱ ደግሞ ሌላ ፈታኝ ነገር ነበር።
ፊትን የሚሸፍነው ማይካ በቀላሉ ገበያ ላይ የሚገኝ ቢሆንም እርሱን አቅፎ የሚይዘው ፍሬም ግን በ3ዲ ፕሪንተር መታተም እንዳለበት ጨምረው ያብራራሉ።
ይህ መሸፈኛውን የሚያቅፈው ፍሬም ፀጉር ላይ እንደሚቀመጥ ቲያራ ዓይነት ሲሆን፣ ተበስቶ የፊት መሸፈኛውን እንዲታሰርበት ይደረጋል።
በ3 ዲ ፕሪንተር ላይ ለማተም ይጠቀሙበት የነበረው ቁስ አንዴ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ እንደማያገለግል የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፣ ልጠቀምበት ቢባል እንኳ በቀላሉ ባክቴሪያ እንደሚስብ በተጨማሪም የአቅርቦት እጥረት መኖር ፈታኝ ማድረጉን ያስረዳሉ።
ይህ የፊት መከለያ ማይካ ከቻይና እንደሚገባ የሚገልፁት ባለሙያው፣ ነገር ግን ግንባር ላይ የሚያርፈው የፊት መሸፈኛ አካሉ ስፖንጅ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህ ደግሞ በቀላሉ ባክቴሪያን ስለሚይዝ በየጊዜው በፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ለማጽዳት አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል።
ነገር ግን ይህንን ከ3ዲ ፕሪንተር ውጪ መስራት አስፈላጊመሆኑን እንዲሁም በአገር ውስጥ በቀላሉ በሚገኝ ቁስ ቢሰራ መልካም መሆኑን ማስተዋላቸው የራሳቸውን የፊት መሸፈኛ ዲዛይን አድርገዋል።
በዚህም ወቅት መሳሪያው ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጎ ቢሰራ መልካም መሆኑን ማስተዋላቸውንም ይገልጻሉ።
በዚህም የተነሳ የሰሩት የፊት መሸፈኛ ዳግም ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ ፊትን የሚከላከለው ማይካ ደግሞ በትንፋሽ አማካኝነት በቀላሉ ጭጋግ አይለብስም ሲሉ ያብራራሉ።
እርሳቸው የሰሩት የፊት መከለያ ወጥ የሆነ ከፕላስቲክ የተሰራ ሲሆን ተቆርጦ በሌዘር ውስጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ለማጽዳት በሚፈለግበትም ወቅት ተፈትቶ በኬሚካል በቀላሉ ለማጽዳት እንዲቻል ተደርጎ መሰራቱን ያስረዳሉ።
እነዚህ መሳሪያዎች ለየት የሚያደርጋቸው በቀላሉ ተፈታትተው መገጣጠማቸው ብቻ ሳይሆን፣ አገር ውስጥ በቀላሉ ከሚገኙ ቁሶች መሰራታቸውም ሌላው ለየት የሚያደርጋቸው ነገር መሆኑን ይገልጻሉ።
አቶ አሸናፊ የሰሩት የፊት መሸፈኛ ቅርፁን ጠብቆ እንዲቆይ እና በቀላሉ እንዳይሰብ ተደርጎ መሰራቱን ጨምረው ተናግረዋል።