ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሌክሲ ናቫንሊ፡ የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ የሩስያ ባለሥልጣኖችን አገደ
ፑቲንን አጥብቆ የሚተቸው አሌክሲ ናቫንሊ በኖቪቾክ መመረዙን ተከትሎ፤ የአውሮፓ ሕብረት ስድስት ከፍተኛ የሩስያ ባለሥልጣኖችን አገደ።
ሕብረቱ ኖቪቾክ ላይ ምርምር የሚያካሂድ ማዕከል ላይም እገዳ ጥሏል።
የአውሮፓ ሕብረት ጉዞ ላይና የገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ እገዳ ከጣለባቸው መካከል የፌደራል ደህንነት ኃላፊ አሌክሳንደር ቦርትኒኮቭ ይገኙበታል።
ሁለት ምክትል የመከላከያ ሚንስትሮችም በእገዳው ተካተዋል። የፑቲን የሳይቤሪያ ልዩ ልዑክ ሰርጌ ሜንያሎም ታግደዋል።
ተቃዋሚው አሌክሲ በርሊን ውስጥ እያገገመ ሲሆን፤ ከመመረዙ ጀርባ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን እንደሆኑ ተናግሯል።
ሩስያ ግን ክሱን አጣጥላለች።
የአውሮፓ ሕብረት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች እገዳው እንዲጣል ተስማምተዋል። በተለይ ፈረንሳይ እና ጀርመን መርዙ ከመንግሥት ተቋም እንደመጣ በማመን እገዳው እንዲጣል ገፋፍተዋል።
"አሌክሲ ናቫንሊ በተመረዘበት ወቅት ክትትል እየተደረገበት እንደነበረ ከግምት በማስገባት ሊመረዝ የቻለው በፌደራል ደህንነት እንደሆነ መደምደም ይቻላል" ሲል ሕብረቱ መግለጫ አውጥቷል።
የአውሮፓ ባለሙያዎችን ድምዳሜ ሩስያ አትስማማበትም።
ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ሩስያ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ያረቀቀችው ኖቪቾክ አሌክሲን ለመመረዝ ጥቅም ላይ ውሏል።
የአውሮፓ ሕብረት እገዳው ኬሚካል መሣሪያን ለማስቆም የሚደረግ ጥረት አካል ነው ብሏል። የሕብረቱ መሪዎች በብራሰልስ የሁለት ቀናት ጉባኤ ያካሂዳሉ።
የሩስያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የአውሮፓ ሕብረት "በመከባበር የተሞላ ውይይትን" አይረዳም ሲሉ ወንጅለዋል። ሩስያ እገዳ ከተጣለባት አጸፋውን እንደምትመልስም አስረግጠዋል።
አሌክሲ የጸረ ሙስና አቀንቃኞችን ይመራል። ነሐሴ ላይ ከሰርቢያ ሲመለስ፣ አውሮፕላን ውስጥ ሳለ መመረዙ ይታወሳል። ከዛም በርሊን በሚገኝ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ማቆያ ውስጥ ነበር።
አገራት የተጣመሩበት የጸረ ኬሚካል መሣሪያ ድርጅት፤ አሌክሲ በኖቪቾክ መመረዙን አረጋግጧል።
የአውሮፓ ሕብረት ሩስያ ጉዳዩን እንድትመረምር እና ከድርጅቱ ጋር እንድትተባበር አሳስቦ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እንደሚለው፤ እአአ 2018 ላይ የቀድሞው ሩስያዊ ሰላይ ሰርጌ ስኪርፓል እና ልጁ የተመረዙት በኖቪቾክ ነው።
አባትና ልጅ አሁን በሚስጥራዊ ቦታ ይገኛሉ።
የአውሮፓ ሕብረት የቭገንሊ ፕሪጎዚን ወይም 'የፑቲን ሼፍ' በመባል የሚታወቁት ነጋዴ ላይ እገዳ እንደሚጥል የጀርመን ሚዲያ ዘግቧል።
ግለሰቡ ወደ ሊቢያ መሣሪያ በማስገባታቸው እገዳ ሊጣልባቸው እንደሚችልም ተጠቁሟል።