"19 ዓመታትን በእስር፣ አሁንም እየቆጠርን ነው" የፔን ተሸላሚው አማኑኤል ወንድም

"አስራ ዘጠኝ አመታት በእስር ፣ አሁንም እየቆጠርን ነው። በጣም ከፍተኛ ህመም አለው" ይህንን የተናገረው በቅርቡ አለም አቀፉን የፔን ሽልማት የተጎናፀፈውና በእስር ላይ የሚገኘው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ አማኑኤል አስራት ወንድም ዳንኤል ነው።

በሰላ ትችቱ የሚታወቀውን ኤርትራዊ ጋዜጠኛ አማኑኤል አስራት ለበርካቶች ደፋር ፀሃፊ ነው።

ለዚህም ነው ፔን በሚፅፉት ወይም በሚናገሩት ነገር የሚደርስባቸውን ጫናና ጣልቃ ገብነት ተቋቁመው የበለጠ ወኔ ላሳዩ ፀሃፊዎች እውቅናን የሚሰጥበትን "አለም አቀፉ ደፋር ፀሃፊ" በሚል ስያሜም ሽልማቱን ያቀናጀው።

ወንድሙን ለሁለት አስርት አመታት ያህል ላላየው ዳንኤል ምንም እንኳን በደንብ ሽልማቱ ይገባዋል ብሎ ቢያምንም ለሱም ቢሆን ለቤተሰቡ ከፍተኛ አድናቆትን እንደፈጠረባቸው አልደበቀም።

ከሽልማቱ ጀርባም አማኑኤል አብሯቸው አለመሆንንም ለቤተሰቡ ማስታወስ የየቀኑ መራር እውነታ ነው።

"በጣም በጣም ከፍተኛ ህመም አለው" በማለትም መሃል ላይ ኃዘኑን በሚያሳብቅ ድምፅ የሚተነፍሰው ዳንኤል

"በነዚህ አመታት ውስጥ ሊያገባ ይችል ነበር፤ ልጆች ያፈራ ነበር። ትምህርቱን መቀጠል ይችል ነበር። ለአገሪቷም በርካታ ትልልቅ ነገሮችን ማድረግ ይችል ነበር። ከዚህ በላይ ህመም የሆነው ደግሞ መቼ እንደሚፈታ አለማወቃችን ነው። በህይወት ይኑርም፣ አይኑርም አናውቅም"ብሏል ኃዘን በተሞላ ድምፁ

አማኑኤል በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በኤርትራ የጋዜጠኝነት ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የዘመን ጋዜጣም ዋና አዘጋጅ ነበር።

በሰላ ትችቱም የሚታወቀው ጋዜጠኛ በወቅቱም በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት መካከል የተፈጠረውን ቅራኔም ይፋ በማውጣት ይፅፍ ነበር።

በተለይም ከመቶ ሺዎች ህይወት በላይ የቀጠፈውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን አጥብቀው ከሚቃወሙት መካከልም ነው። ይህንኑም በፅሁፉ ላይ ያንፀባርቅ ነበር።

ለፔን ሽልማትም ያበቃው ስለ ጦርነት አስከፊነት የሚያወሳበት ግጥሙ ነው።

በዚህ ግጥሙም ምን ያህል ጦርነቱ የሁለት ወንድማማቾችና ቤተሰቦች ጦርነት እንደሆነም በተመረጡ ቃላቶች ያስታውሳል። በርካታ ቤተሰቦችን ልጅ አልባ፣ ወንድም አልባ፣ ባለቤት አልባ አድርጓል፤ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ቀጥፏል።

የጦርነቱን አስከፊነትና አስቀያሚነት አማኑኤል ሲያወሳም በሰላማዊ መንገድ ተደራድረው መፍታት የሚችሉትንና ፣ ጦርነት የመረጡትን ሁለቱንም መንግሥታት ይተቻል።

ይህ የሰላ ትችቱ ግን ዋጋ ያስከፈለው ሲሆን ኤርትራም የግል ጋዜጦችን ዘጋች እንዲሁም የሚቀርቡበትን ትችት ዝም ለማሰኘት በጀመረው ዘመቻም የኤርትራ መንግሥት ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ተማሪዎችን ለእስር ዳርጓል።

አማኑኤልን ጨምሮ በርካታ የግል ጋዜጣ አዘጋጆችም በጎሮጎሳውያኑ 2001 ለእስር ተዳረጉ። አማኑኤልም ሆነ ሌሎች ፀሃፊዎች ያሉበት ሁኔታ የማይታወቅ ሲሆን እስካሁንም ያናገራቸው አካል የለም።

ቤተሰቦች ድምፁን ሰምተው አያውቁም፤ ያለበትንም አያውቁም።

"የኤርትራ መንግሥት አምባገነን ነው። መንግሥቱ ከሌሎች ለየት ያለ ነው። እንደ መንግሥት ደንብና አወቃቀር የለውም። ኤርትራ የምትመራው በአንድ ሰው ነው።በአገሪቱም ያለው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ አንድ ሚዲያ ነው " የሚለው ዳንኡል

ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናትም ቢሆኑ አማኑኤልን ሆነ ሌሎች እስረኞች ያሉበትን ቦታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተው ስለማያውቁም "ቤተሰቦቼ፣ ዘመዶቼ የት ነው የታሰሩት ተብሎ መጠየቅ አይቻልም፤ የሚጠየቅ አካልም የለም፤ ፖለቲከኛም ሆኑ ጋዜጠኛ" በማለት ዳንኤል ያስረዳል።

አማኑኤል ሁለገብ ነው፤ ከጋዜጠኝነትም በላይ ገጣሚ፣ የሙዚቃ ግጥም ፀሃፊ፣ ሂሰኛና የሌሎችም ድርብርብ ባለሙያ ነው።

ለሁለት አስርት አመታት የሚጠጋ በእስር ላይ የሚገኘው አማኑኤልን ጨምሮ ጥቂት ፀሃፊዎች በህይወት እንዳሉና በእስርም ላይ እንደሚገኙ ይታመናል።ታሳሪዎቹ ምንም ክስ እንዳልቀረበባቸውና መንግስትም መረጃ እንደማይሰጥ የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች ይገልጻሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የህክምና አቅርቦት ማጣት እንዲሁም ሌሎች እንግልቶችና ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ ይታመናል።

ገጣሚ አማኑኤል ለዚህ ሽልማት ያጨው ጃማይካዊ- ኢንግሊዛዊ ገጣሚ ሊንቶን ክዌሲ ጆንሰን "አንድ ዜጋ ፍጹም በማይታወቅ እስር ቤት ለ20 አመታት ማጎር የአምባገነን ስርአት ማሳያ ነው። በአፍሪካዊ ዲያስፖራነቴ ትብብርና ወገንተኝነቴን ለማሳየት ደግሞ ይሄን ሽልማት ለገጣሚ አማኑኤል አስራት እንዲሸለም መርጫለሁ" ማለቱን ፔን ኤርትራ ገልጿል። በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፈው የአማኑኤል ወንድም ከጋዜጠኛው ስራዎች አንዱ የሆነውን ግጥምም አቅርቧል።

አማኑኤል አስራት በ2016 ከሌሎች ግብጻዊና ቱርካዊ ጸሃፍያን በመሆን በፔን ኦክስፋም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት ተሰጥቶታል።