ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንበጣ መንጋ፡ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ ሄሊኮፕተር ተከሰከሰ
በአማራ ክልል ወረባቦ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ ሄሊኮፕተር ዛሬ መስከረም 22/2013 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡30 ላይ በወረዳው 014 ቀበሌ ልዩ ስሙ ፍራንጉል በሚባል ቦታ መከስከሱ ተገለጸ።
የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳዳም ሽመልስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአደጋው በሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንና የሄሊኮፕተሩ አብራሪ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት በሰመራ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።
ኃላፊው የአደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአንበጣ መንጋው ከዚህ በፊት ከተከሰተው በበለጠ በወረዳው 6 ቀበሌዎች መከሰቱን የገለፁት አቶ ሳዳም፤ አንበጣው በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኃላፊው እንዳሉት አንበጣውን ለመከላከል የአካባቢው ነዋሪዎች ባህላዊ መንገዶችን ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን፤ በሄሊኮፕተር የኬሚካል ርጭት የተጀመረው ባለፈው ቅዳሜ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሰመራ የሚነሳው ሄሊኮፕተርም በየሁለት ቀኑ ገደማ የኬሚካል ርጭት ሲያደርግ እንደነበር ተናግረዋል።
የአንበጣ መንጋው በወረዳው ከ5 ሺህ ሔክታር በላይ ሰብል ያወደመ ሲሆን፤ እስከ ትናንት ድረስ ከ14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የኬሚካል ርጭት መደረጉንም ኃላፊው ገልፀዋል።
የአንበጣ ወረራው አስጊ እንደሆነም ኃላፊው አክለዋል።
ሚያዚያ ወር ላይ ከሶማሌላንድና የመን እንደተነሳ የተነገረው የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ተከስቶ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል። አሁንም በድጋሚ የተከሰተው የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው።
የአንበጣ መንጋን በባህላዊ መንገድ እንዴት መከላከል ይቻላል ?
ማኅበረሰቡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ድምፅ የሚፈጥሩ ነገሮችን በማቃጨል፣ በጅራፍ፣ በጥይት፣ በጩኸት፣ በርችት፣ በዘፈን፣ በፉጨት፣ ጨርቅ በማውለብለብ ለመከላከል ሲሞክሩ ተስተውለዋል።
ይህንን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶን ለቢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።
አቶ ዘብዲዮስ አንበጣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ አይደለም በማለት አንበጣን በባህላዊ መንገድ መከላከል በሳይንስም የሚደገፍ ነው ይላሉ።
ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር አካባቢና ከዚያ ባሻገር ካሉ የአረብ አገራት የአንበጣ መንጋ ይመጣ ስለነበር አንበጣን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ልማድ እንደነበር ይናገራሉ።
አንበጣው ሰብል ላይ እንዳያርፍ የማባረር ሥራም ይሠራ ነበር። ነገር ግን ከቦታ ቦታ የመረጃ ልውውጥ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ወደ ሄደበት አካባቢ ሪፖርት ማድረግ መዘንጋትም የለበትም ይላሉ።
ይሁን እንጅ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች አንበጣን በጥይት ለማባረር የሚደረገው ሙከራ ትክክል አይደለም ሲሉ ነቅፈዋል- በጥይት የማባረር ተግባር ከአራት ዓመታት በፊት ጉዳት እንዳስከተለም ያስታውሳሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ በወቅቱ ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ መከላከል አምልጦ ወደ አዲስ አበባ የገባው በጥይት ምክንያት ነው። ከዚያም ወደ ሰሜን የአገሪቷ ክፍሎች አምርቶ በርካታ ቀበሌዎችን ማዳረሱ የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው።
በመሆኑም "ብዙ ጭስ ማጨስ ሳያስፈልግ፤ በጭስ፣ በቆርቆሮ ድምፅ፣ በልጆች ጩኸት ድምፅ፣ በተለይ በጅራፍ ከሰብል ላይ መንጋውን ማባረር በቂ ነው" ሲሉ ይመክራሉ።
ነገር ግን ከሰብል አቅራቢያ ያለ የግጦሽ መሬት ላይ፣ ደን አካባቢ እና ሌሎች አካባቢዎች ሄዶ ካረፈ ማደሪያውን ብቻ መከታተል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
በርካታ ሕዝብ የማይኖርበትና ለመጠጥና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች ባሉበት ቦታ ካልሆነ በስተቀር ፀረ ተባይ ኬሚካል መርጨት እንደሚቻል አቶ ዘብዲዎስ አስገንዝበዋል።