ኦሮማራ ፡ የአማራና የኦሮሞ ፓርቲዎች ስምምነት ተሳታፊዎች ምን ይላሉ?

የአማራ እና የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላለፉት 10 ወራት ስንወያይባቸው ነበሩ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ውይይቱ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ህዳር እና ጥቅምት ወር አካባቢ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ጠቅላይ ሚንስትሩ የኦሮሞና የአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመሰብሰብ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲመጣ ውይይቶች መጀመራቸውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር አቶ በለጠ ሞላ ተናግረዋል።

መንግሥት ውይይቱ በማመቻቸት ከሁለቱም ብሔሮች የመድረኩ አዘጋጆች ተመርጠው ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ከእዚህ አንጻር የሚያስማሟቸውን ነጥቦች እየለዩ የማያስማሟቸውን ደግሞ ለጊዜው ወደ ጎን በማስቀመጥ 10 ነጥቦች ላይ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

"ከመጀመሪያው የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ውይይት በኋላ ታኅሳስ ላይ ትልቅ ውይይት አድርገን ሁላችንም የአቋም መግለጫ አውጥተን እርሱን መነሻ አድርገን፣ ቀጣዮቹን ውይይቶች አካሂደናል" ይላሉ አቶ በለጠ።

በአጠቃላይ 10 የሚጠጉ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው እንደነበር የተናገሩት አቶ በለጠ "አዘጋጆች ቀድመው የምንወያይበትን አጀንዳ እየላኩልን በተያዘው አጀንዳ ላይ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ነው ውይይቱ የተካሄደው" ብለዋል።

ከተደረሱት ስምምነቶች በተጨማሪ እንደእዚህ አይነት የፖለቲካ ባሕል በኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር መጀመሩ በራሱ ቀላል ትርጉም የሚሰጠው አለመሆኑን አቶ በለጠ ይገልጻሉ።

"የተስማማንባቸውን ነጥቦች ሁላችንም ወደንና ፈልገን ያመጣናቸው ናቸው፤ ስለዚህ ለተግባራዊነታቸው ሁላችንም መጣር አለብን፤ የአዳራሽ ስምምነት በቂ አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ማስተግበር ይኖርበታል" ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ ኃላፊነት በመሆኑና ብዙ የተደከመበትም ስለሆነ ሁሉም ስምምነቶች በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ይተገበራሉ የሚል እምነት መኖሩን የተናገሩት አቶ በለጠ፣ መንግሥትንም የመወትወት እና ግፊት የማድረግ ሥራ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ፓርቲያቸውም ስምምነቶቹን ለማክበርና ለተግባራዊነታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከተሳትፎ አንጻር በአብዛኛው ሁሉም ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጸው፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲዎችም በዝርዝሩ ውስጥ መኖራቸውን ያስታውሳሉ። ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ሙህራን እና ሌሎች ይመለከታቸዋል የተባሉ ባለድርሻ አካላትም የውይይት መድረኩ ተሳታፊ ነበሩ።

ከመጋቢት በፊት በነበሩት መድረኮች እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ እስከ 25 ሰው በመላክ ውይይት ተካሂዷል።

በመጀመሪያዎቹ መድረኮች ብዙ ሃሳቦች ያለገደብ መነሳታቸውን የሚያስታውሱት አቶ በለጠ በቀጣይ ደግሞ ሃሳቦችን በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ በመለየት "ቅድሚያ የምንሰጠውንና የተስማማንበትን እየለየን፣ 10ሩ ላይ ተስማምተናል። እኛም እነሱም ያልተስማማንባቸው ብዙ ሃሳቦች አሉ፤ በቀጣይ ልንስማማባቸው እንችላለን፣ ባንስማማ እንኳ ሁለታችንም ግማሽ መንገድ እንሄዳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

"እኛ እንደ ድርጅት ብዙ ሥራዎችን ብንሰራም ከሁለት ዓመት ያልዘለለ እድሜ ያለን ነን። በዚህ ደረጃ መወያየታችንና በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ተወያይተን የሚያግባባ ስምምነት ላይ መድረሳችን ተደማጭነታችን ማደጉንና ለሰላም የምንከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው" በማለት አብን የነበረውን ሚና ይናገራሉ አቶ በለጠ።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳን፤ ስለምን የአማራና የኦሮሞ ብሔር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች በዚህ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ ተፈለገ ስንል ጠይቀናቸው ነበር።

ጉዳዩ ኦሮሞና አማራን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ቢሆንም እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች በመካከላቸው ትልቅ ትስስር አለ በማለት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ፓርቲዎች ከተስማሙ ቀጥሎ ለሚካሄደው ሌሎችን ብሔር ብሔረሰቦች የሚያሳትፍ ስብሰባ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ መፍጠር ይችላል ተብሎ ስለታመነበት ቅድሚያ እንደ ተሰጠው ተናግረዋል።

የዚህ አገር ፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛውን ጊዜ ስለ አማራ እና ኦሮሞ የሚሰሩት ሕዝቡን አንድ በሚያደርግ ላይ አይደለም ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ ይህ ደግሞ ሕብረተሰቡ ላይ ትልቅ ጫና ስለሚፈጥር ለዚያ ነው ይህንን አስቀድመን በትኩረት ልንሰራበት የወሰንነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኦፌኮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገምታ በበኩላቸው ረቡዕ በተካሄደው ጉባዔ ላይ ከኦፌኮ የተሳተፈ ሰው የለም ሲሉ ተናግረዋል።

"በፊርማው ሂደት ውስጥም አልተሳተፍንም የተፈረመው ነገርም እኛን አይመለከተንም" በማለት ሰዎች ዝም ብለው በራሳቸው ፍላጎት የፓርቲያቸውን ስም አንስተው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

"ስለጉዳዩ መረጃ ነበረን ሆኖም ግን ስብሰባ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ስላልነበረን አልተሳፍንም" ያሉት የኦፌኮ አመራር አባል በስብሰባው ለደጋፊዎቻቸው፣ አባላቶቻቸውና ለሕዝቡ አንዳች ጥቅም እናስገኝበታለን ብለው በማመን በመጀመሪያ ላይ መሳተፋቸውን ቢገልጹም "ያመጣው ውጤት የለም" ብለዋል።

"የሕዝባችንን ጥቅም የማያስከብር፣ የፓርቲያችን ራዕይ ማስኬድ የማንችልበት ጉዳይ ላይ መሳፈተፍ ፍላጎታችን ስላልሆነ ራሳችንን አግልለናል።"

ወደፊት ለአገራችን ፋይዳ በሚኖረው ስብሰባ ላይ እንሳተፋለን ያሉት የኦፌኮ አመራር አባል አቶ ጥሩነህ፤ "ይህችንም አገር የሚያድናት ውይይት ነው ብለን እናምናለን" ብለዋል።

አሁን በሁለቱ ብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጀመረው የሁለትዮሽ ውይይት ቀጣይ ደግሞ ከአማራ እና ኦሮሞ በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ የሚሆንበት ሰፊ መድረክ ይዘጋጃል ብለን እናስባለን ያሉት አቶ በለጠ፤ ለ10 ወራት የተካሄደው ውይይትም አዘጋጆቹ በሚያቀርቡት መነሻ መሰረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።