ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካናዳ ፡ የመጀመሪያው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐውልት በተቃዋሚዎች ተገረሰሰ
በሞንትሪያል ካናዳ ተቃዋሚዎች የሰር ጆን ኤ ማክዶናልድን ሐውልት ገረሰሱ፡፡
ሰር ማክዶናልድ የካናዳ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስተር ናቸው፡፡
ሰውየው በሥልጣን በነበሩበት 19ኛው ክፍለ ዘመን የአገሬውን ነዋሪ ሰዎች በመጨፍጨፍ ታሪክ ይጠቀሳሉ፡፡
አንድ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለ ቪዲዮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐውልት ከነበረበት ማማ በአፍጢሙ ሲተከልና ወደ መንገድ ተንከባሎ ሲሄድ የሚያሳይ ነው፡፡
የኩቤክ የመንግሥት ተጠሪ ድርጊቱን "ተቀባይነት የሌለው" ብለውታል፡፡
‹የታሪካችንን አካል ማጥፋት መፍትሄ አይደለም› ብለዋል የኪቤት አስተዳደር ፍራንኮይስ ሊጎት፡፡
የካናዳዊ ሲቢኤስ እንደዘገበው እስካሁን ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ የለም፡፡
ሰር ማክዶናልድ እንደነሱ አቆጣጠር ከ1860ዎቹ እስከ-1890ዎቹ በአመራርነት የቆየ ሲሆን በአገር ግንባታ ፖሊሲዎቹ የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም ሪዚደንሻል ስኩል ሲስተም የሚባል የአዳሪ ትምህርት ቤት አሰራርን በመቅረጽ አግላይ ፖሊሲን ተግባራዊ አድርጓል ተብሎ ይተቻል፡፡
ለመቶ ዓመት ያህል ተግባራዊ በሆነው በዚህ ፖሊሲ 150ሺ ነባር የአገሬው ተወላጅ ቤተሰብ ልጆች ከቤታቸው ተፈናቅለው በመንግሥት የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ብቻ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርገዋል፡፡
የነባር አገሬው ልጆች በዚህን ጊዜ በቋንቋቸው እንዳይናገሩ፣ ባህላቸውን እንዲጫኑ ተደርገዋል፡፡ በርካቶችም በዚህ ወቅት ለሞት ተዳርገዋል፡፡
መንግሥት በ2015 ራሱ እንዳመነው ያ የትምህርት ፖሊሲ ‹‹የባሕል ጭቆናና የባህል ዘርፍ ፍጅት›› ተብሎ መጠራት ያለበት ስሁት ተግባር ነበር፡፡
ማክዶናልድ በዚያ ዘመን ነባር የአገሬው ሰዎችን ሆን ብሎ በማስራብ እንዲሁም በበሽታ እንዲያዙ በማድረግ ከዚያ አገር እንዲጠፉ አድርጓል በሚል ይከሰሳል፡፡
ሐውልቱን የገረሰሱት የመብት ተቆርቋሪዎች የመጀመርያው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር የነጭ አክራሪ ብሔርተኛ፣ ባሕል ጨፍላቂና የዘር ፍጅትን የፈጸሙ ወንጀለኛ ናቸው ይላሉ፡፡
ለሞንቴሪያል ከንቲባ ከዚህ ቀደም ሀውልቱ እንዲፈርስ ፊርማ ተሰብስቦ ተግባራዊ ሊያደርጉት ስላልቻሉ ግዴታችን ተወጥተናል ብለዋል ተቃዋሚዎቹ፡፡
የጆርጅ ፍሎይድን የግፍ ግድያ ተከትሎ በዓለም ላይ በባርነትና ዘረኝነት የሚታወቁ ‹ጀግኖች› ሐውልቶች በበርካታ ከተሞች እንዲፈርሱ ሆነዋል፡፡
በአሜሪካ የክርስቶፎር ኮሎምቦስ ሐውልት እና የኮንፌዴሬት ባሪያ አሳዳሪ የነበሩ መሪዎች ሐውልቶች የፈረሱ ሲሆን በዩኬ የባሪያ ንግድ ያስፋፉ መሪዎች ሐውልቶች ተገርስሰዋል፡፡
በቤልጂየምም ተቃዋሚዎች በተመሳሳይ የንጉሥ ሊዮፓርድ ዳግማዊን ሐውልት ጉዳት አድርሰውበታል፡፡ ሊዮፓርድ ዳግማዊ በአሁኗ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባደረሰው ግፍ ነው ተቃውሞው የተነሳበት፡፡
ኮንጎ ያን ጊዜ የንጉስ ሊዮፓርድ ዳግማዊ የግል ሀብቱ ነበረች፡፡