ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ 7 ጥይት የተተኮሰበትን ጥቁሩን ጃኮብ ሆስፒታል ሄደው ሊጠይቁት ይሆን?
የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ዊስኮንሰን ግዛት የምትገኘውን ኬኖሻ ከተማን ሊጎበኙ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ጆኮብ ብሌክ የተባለ ወጣት ጥቁር በ7 ጥይት በፖሊስ ከፍተኛ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ በኬኖሻ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡
ትራምፕ ወደ ኬኖሻ የሚሄዱት ከነገ በስቲያ ማክሰኞ እንደሆነ ዋይት ሐውስ ይፋ አድርጓል፡፡
ትራምፕ እዚያ ሄደው ምን እንደሚያደርጉ በዝርዝር ባይገለጽም ከጸጥታ አስከባሪ አካላት ጋር ይነጋገራሉ፤ የደረሰውን ጉዳት ይገመግማሉ ተብሏል፡፡
ጥቁሩ ጃኮብ ብሌክ 7 ጥይት በጀርባው ተተኩሶበት በሕይወት መትረፉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
አከርካሪው ላይ አንዲት ጥይት በመሰንቀሯ ህብለሰረሰሩ ተጎድቷል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ቆሞ መራመድ አይችልም ተብሏል፡፡
የጃኮብ ጉዳትን የሚያሳየው ቪዲዮ ማኅበራዊ ድራምባው ከተጋራ በኋላ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡
በኬኖሻ ዊስኮንሰን የነበረው ተቃውሞ ግን በዝርፍያና በነውጥ የታጀበ ሲሆን የሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል እየተባለ ነው፡፡
በርካታ መኪናዎችም ወድመዋል፣ ሱቆች ተዘርፈዋል፤ በእሳት ተያይዘዋል፡፡
ባለፈው ግንቦት ወር በሜኔሶታ፣ ሚኒያፖሊስ ከተማ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ አንድ ጥቁር በነጭ ፖሊስ ማጅራቱ ተቆልፎ እንዲሞት ከሆነ በኋላ የጥቁሮች የመብት እንቅስቃሴ በመላው ዓለም እየተፋፋመ ይገኛል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ጃኮንብ ይጎበኙታል?
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ጃኮብን ይጎበኙት ይሆን የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡
አሁን ለጊዜው የታወቀው የከተማዋን ፖሊስ እንደሚያነጋግሩና በነውጡ የደረሰውን የጉዳት መጠን እንደሚብራራለቸው ነው፡፡ ይህን የተናገሩት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጁድ ዲር ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ የጥቃቱን ሰለባ የሆነውን ጃኮብ ብሌክንና ቤተሰቦቹን ይጎበኛሉ ወይ በሚል ለቃል አቀባዩ ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበረ ሲሆን ይህን ለመናገር ገና ዝርዝር የጉብኝት እቅድ መረጃ ያስፈልገኛል ብለዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በጥቁሮች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በግልጽ ሲኮንኑ ብዙም አይሰሙም፡፡ እሁድ ለታ በጃኮብ ብሌክ የደረሰውን ጥቃትም በቀጥታ አላወገዙም፡፡
በጃኮብ ላይ የተኮሰው ፖሊስ መከሰስ አለበት ወይ በሚል አርብ ዕለት አንዲት ጋዜጠኛ ጥያቄ አቅርባላቸው ነበር፡፡ ‹‹ ገና ሪፖርት አልቀረበልኝም፤ ነገሩን ማጤን አለብኝ፡ ቪዲዮውን አይቼው ግን አልወደድኩትም›› ብለዋል፡፡
ትራምፕ በመጪው ኅዳር በሚጠብቃቸው ምርጫ ‹‹ሥርዓት ማስከበርን› እንደ አጀንዳ ይዘው እንደሚሰሩበት ተናግረዋል፡፡
‹ዲሞክራቶች በሚበዙባቸው ከተሞች ሥርዓት አልበኝነት ነግሷል፣ ዙርፊያ ተጧጡፏል፣ ፖሊሶች እየተጎዱ ነው ፤ ስለዚህ ይህን ጋጠወጥ ሁላ ልክ አስገባዋለሁ› ብለው ሲዝቱም ነበር፣ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት፡፡
ከምርጫ ጋር በተያያዘ ዊስኮንሰን ግዛት ‹ወላዋይ› ከሚባሉ ግዛቶች አንዷ ናት፡፡
ግዛቷ ቀድሞ ባራክ ኦባማ ያሸነፉባት በመሆኑ የዲሞክራቶች ግዛት ብትመስልም ትራምፕ በ2016 በ20ሺ ድምጽ ብልጫ ሂላሪን ማሸነፋቸው ደግሞ ወላዋይነቷን የሚያሳይ ነው፡፡
በኬኖሻ ከአንድ ሺ በላይ ሰልፈኞች ‹የጥቁር ነፍስ ዋጋው ስንት ነው?› በሚል ቅዳሜ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡
የጃኮብ አባት ሰልፈኞች ከነውጥ፣ ከጥቃትና ካያልተገባ ድርጊት ራሳቸውን እንዲያቅቡ አደራ ብለዋል፡፡
በኬኖሻ ከ1ሺ በላይ የብሔራዊ ጥበቃ ልዩ ኃይል እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ብዙዎቹ ታዲያ ከሌላ ግዛት የመጡ የልዩ ጥበቃ አባላት ናቸው፡፡