ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የባሪያ ፈንጋዮችን ሐውልት መፈንገል ታሪክን ጭምር መደምሰስ ይሆን?
የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በርካታ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል።
"የጥቁር ነፍስ ዋጋዋ ስንት ነው?" የሚሉ እሮሮዎች በመላው ዓለም ተቀጣጥለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ፣ በኔዘርላንድስ፣ በፈረንሳይና በጣሊያን የዘረኞችና ባሪያ ፈንጋዮች ሐውልቶች ፈርሰዋል፤ ወይም እንዲፈርሱ ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።
በቅርቡ እንኳ በጣሊያን ሚላን ከተማ አንዲት የ12 ዓመት ኤርትራዊትን በባሪያነት ገዝቶ ያሳድር የነበረና ለሙሶሎኒ ወረራ ኢትዮጵያ ድረስ ዘምቶ ቅኝ ግዛትን ሲያሞካሽ የኖረ ጋዜጠኛ ሐውልት በተቃዋሚዎች ጥቃት ደርሶበታል።
ይህ ሐውልት እንዲፈርስ ከፍተኛ ግፊት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የሚላን ከተማ ከንቲባ ግን "ይህ ጣሊያናዊ ሐውልት የቆመለት ለቅኝ ግዛት ጥብቅና በመቆሙ ሳይሆን ለፕሬስ ነጻነት በነበረው ቁርጠኝነት ነው፤ ሰዎች ሙሉ አይደለንም፤ ሁላችንም ድክመቶች እንዳሉብን አንርሳ" ሲሉ ተከራክረውለታል።
ይህ ክርክር ታዲያ ወደ ኦክስፎርድም ጎራ ያለ ይመስላል።
የባሪያ ፈንጋዮችን ሐውልት መፈንገል ታሪክን ጭምር መደምሰስ ይሆን?
እጅግ ላቅ ያለ አእምሮን የታደሉ በብዛት የሚታደሙባቸው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ካምፓሶች ከሰሞኑ በዚህ ክርክር ተጠምደው ነው የሰነበቱት።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የኦሪያል ኮሌጅ ለተከታታይ ቀናት በቆየ ተቃውሞ የዝነኛውን የአፓርታይድ አባት የሴሲል ጆን ሮደስ ሐውልትን ለማፍረስ ከውሳኔ እንደደረሰ ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
ሮደስ ከ1853-1902 የኖረ እንግሊዛዊ ሲሆን የማዕድን ቁፋሮ ኩባንያ ባለቤት፣ ፖለቲከኛና የደቡብ አፍሪካ አካባቢ ቅኝ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ ሰው ነበር። የእርሱ ኩባንያና የእንግሊዝ መንግሥት ዚምባቡዌና ዛምቢያን ጨፍልቆ የሮዴሺያ ግዛት አድርጎ ሲገዛቸው ነበር።
ሰውየው ባሪያ ፈንጋይ፣ የአፓርታይድ አቀንቃኝ ይሁን እንጂ ጥቁሮችን እየበዘበዘም ቢሆን በርካታ ልማት ውስጥ ተሳትፏል። በደቡብ አፍሪካ በስሙ የተሰየመ ዩኒቨርስቲ ዛሬም ድረስ አለ።
የእርሱ ኩባንያ በገንዘብ የሚደግፋቸው የትምህርት ዕድሎች (ስኮላርሺፕስ) ለበርካታ አፍሪካዊያን ብርሃን እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል።
የአንግሎ ሳክሰን ዘር ዓለምን በወረረ ቁጥር ጨለማ ውስጥ ላሉ የዓለም ሕዝቦች ብርሃን ይፈነጥቃል ብሎ በግልጽ ዘረኝነት ፍልስፍና ደቡባዊ አፍሪካን ሲያምስ የነበረ ሰው ነው።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ኦሪየል ኮሌጅ ካምፓስ ፎቅ ላይ የእርሱ ሐውልት ተለጥፎበት ይገኛል። የዚህ ባሪያ ፈንጋይ ባለጸጋ ሐውልት ይፍረስልን ያሉ ሰልፈኞች በመጨረሻ ምላሽ አግኝተዋል።
ትናንት ረቡዕ ድምጽ የሰጡት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ አስተዳዳሪዎች የሰውየው ሐውልት የኢምፔሪያሊዝምና የዘረኝነት ምልክት ሆኖ መቆየት ስለሌለበት እንዲፈርስ ድምጽ ሰጥተዋል።
ይህ ውሳኔ ታዲያ በቀላሉ የመጣ አይደለም። ለዘመናት የዚህ ሰው ሐውልት እንዲፈርስ ጥያቄ ሲቀርብ ነበር።
ጉዳዩም በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎችን ሲያከራክር የኖረ ነው።
የኦሪየል ኮሌጅ ገዥ "እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከጥልቅ ክርክርና የሐሳብ መንሸራሸር በኋላ ነው፤ ውሳኔያችን በተቀረው ዩናይትድ ኪንግደምና በሌላውም ዓለም የሚኖረውን ትርጉምና ተጽእኖም እንረዳለን" ብለዋል።
ዩኒቨርስቲው ሐውልቱን የማፍረስ ውሳኔውን ተከትሎ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አቋቁሟል። የእዚህ ኮሚሽን ተግባር ደግሞ የሮደስን ውርስ መፈተሸ ነው። በምርመራው መጨረሻ ምናልባትም ከዚህ ሰውዬ ኩባንያ ይገኝ የነበረና በስሙ የተቋቋመውን የትምህርት ችሮታ (ሮደስ ስኮላርሺፕ) እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል።
ይህንን ኮሚሽን የሚመሩት ካሮል ሶተር ምናልባትም ይህ የትምህርት ዕድል ችሮታ ሙሉ በሙሉ ለጥቁር ተማሪዎች እንዲሰጥ ከተማሪ ተወካዮች እና ከከተማው አስተዳደር ጋር ልንመክርበት እንችላለን ብለዋል።
ሱሳን ብራውን የኦክስፎርድ ከተማ ካውንስል ተመራጭ ናት። የሐውልቱን መፍረስ ትደግፋለች። ምናባት ኮሚሽኑ ይህ ሐውልት ከዚህ ተነስቶ ሌላ ተገቢ የሚባል ቦታ ሊፈልግለት ይችላል ሲሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የዚህ የሮደስ ሐውልት ጉዳይ የታሪክ አዋቂዎችንም ለሁለት ከፍሏል።
ውሳኔው ሲጠበቅበት በነበረበት ዕለት ረቡዕ የዩኒቨርስቲው ዲን የሮደስን ሐውልት ማፍረስ ስሜት የማይሰጥ ተግባር ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር።
ዲን ሚሼል ዶነላን እንደሚሉት "ይህ እርምጃ ተራ ስሜታዊነት ብቻም ሳይሆን አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ውሳኔ ነው።"
ሐውልት ማፍረስ ለእኔ ታሪክ ላይ አርትኦት ማድረግ ነው። ታሪክ እንዳለ ይቀመጣል እንጂ አርትኦት አይደረግበትም ብለዋል።
"አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ዘረኝነት አስቀያሚ ነገር ነው፤ የትም መቼም ልናስወግደው ይገባል። ነገር ግን በታሪካችን ውስጥ ነውሮችን ፍቀን ልንወለውል ተገቢ አይደለም" ብለዋል።
ዶ/ር ሚሼል ጨምረው ሲናገሩ ታሪክን መወልወል ትክክል መስሎ ስላልታየኝ የሮደስን ሐውልትን ማፍረስ እቃወማለሁ ብለዋል።
ሴትየዋ በዊልያም ገላድስተን መታሰቢያ ሕንጻ ስም መቀየርም አይስማሙም። ግላድስተን የ19ኛው ክፍለ ዘመን የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ ሲሆን ቤተሰቦቼ በባሪያዎች የሚታረስ እርሻ ስላላቸው የባሪያ ንግድ መቅረት የለበትም ብሎ ሽንጡን ገትሮ የተከራከረ ፖለቲከኛና ነጋዴ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር።
የኦክስፎርድ ሰልፈኞች መከራከርያ ደግሞ እነዚህ ባሪያ ፈንጋዮች የሚወክሉት መልካም ነገር አይደለም፤ ከዚህ ወቅት ጋር የሚሄድም አይደለም። ስለዚህ መወገድ ይኖርበታል ነው።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ምክትል ቻንስለር ሉዊስ ሪቻርድሰን በበኩላቸው የባሪያው ፈንጋዩን የሮደስን ሐውልት ማፍረስ እምብዛምም የደገፉት አይመስም።
በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት "የታሪክ ጉድፎችን መደበቅ መጀመር ወደ አብርሆት መንገድ አይመራንም" ብለዋል።
አንድ የታሪክ ኩነትን ስንረዳ ኩነቱ የተፈጸመበትን ወቅት፣ ሁኔታና ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ማገናዘብ ካቆምን ድምዳሜያችን ሁሉ የተሳሳተ ይሆናል ይላሉ ሪቻርድሰን።
ይህንን ክርክራቸውን ሲያዳብሩ ራሳቸው የሚመሩትን ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲን ይጠቅሳሉ።
"ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ከተመሰረተ ወደ 900 ዓመታት ሆኖታል። ከዚህ ውስጥ ለ800 ዓመታት ያህል በዚህ ዩኒቨርስቲ ሲመላለስ የነበረ ምሁር ነኝ ባይ ሁላ ሴቶች ትምህርት የሚገባቸው ፍጡሮች ስላልሆኑ ዩኒቨርስቲ መግባት የለባቸውም ብሎ የሚያምን ነበር። በዚህ ስሌት ከሄድን እነዚህን ሁሉ ማውገዝ አለብን ማለት ነው?"
"በግሌ ለዚህ የምሰጠው መልስ ማውገዝ የለብንም የሚል ነው። ይመስለኛል በዚያ ዘመን የነበሩ ምሁራን አመለካከታቸው የተዛነፈ ነበር። ነገር ግን ሊመዘኑ የሚገባው በዚያ ዘመን አስተሳሰብና ገዢ ፍልስፍና ነው እንጂ በዛሬ እንዴት ሊሆን ይችላል?" ሲሉ ክርክራቸውን ይቋጫሉ፤ የታላቁ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ሪቻርድሰን።
እውን ሪቻርድሰን እንደሚሉ የባሪያ ፈንጋዮችን ሐውልት ስንፈነግል ታሪክንም አብረን እየደመሰስን ይሆን?