ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሚዲያ፡ ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ከእስር ተለቀቀ
ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ከእስር ተለቆ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ገብቷል።
የሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንዱ ነበር።
በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የእስር ቆይታውም በኮሮናቫይረስ መያዙ ተረጋግጧል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጠኛው የተፈታው በኢትዮጵያ የሚገኘው የአገራቸው ኤምባሲ ጣልቃ ገብቶ እንደሆነ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ የጋዜጠኛውን እስር በመቃወም በርካታ ደብዳቤዎች መፃፉንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ያሲን ጁማ ከእስር እንዲለቀቅ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ከዚህ ቀደም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ነሐሴ 1 በዋለው ችሎት ያሲን ጁማን ጨምሮ የ11 ሰዎች የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በዋስ እንዲወጡ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ፖሊስ ያሲን ጁማን በሌላ የወንጀል ደርጊት ጠርጥሬያለሁ በማለቱ ያሲን ጁማ በእስር ቆይቷል።
የጠቅላይ አቃቤ ህግ ከሰሞኑ በአስቸኳይ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከያሲን ጁማ በተጨማሪ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአሥራት ሚዲያ ጋዜጠኞችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ከእነዚህም መካከል የኦኤምኤኑ ጋዜጠኛ መለሰም ከዚህ ቀደም የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት ከእስር እንዲወጣ ቢወስንም ፖሊስ በሌላ የወንጀል ድርጊት ጠርጥሬዋለሁ በማለቱ ከእስር ሳይለቀቅ ቀርቷል።