ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኬንያዊው ጋዜጠኛ ከእስር እንዲወጣ አዘዘ
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኬኒያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ በአስቸኳይ ከእስር እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጠ።
ያሲን ጁም ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አንዱ ነው።
ከዚህ ቀደም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ነሐሴ 1 በዋለው ችሎት ያሲን ጁማን ጨምሮ የ11 ሰዎች የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በዋስ እንዲወጡ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ፖሊስ ያሲን ጁማን በሌላ የወንጀል ደርጊት ጠርጥሬያለሁ በማለቱ ያሲን ጁማ በእስር ቆይቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ያሲን ጁም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሳለ በኮሮናቫይረስ መያዙ ተነግሯል።
የያሲን ጁማ ጠበቃ የሆኑት አቶ ከድር ቡሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ያሲን በኮቪድ-19 በመያዙ በኢትዮጵያ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ጋዜጠኛው ተለይቶ የሚቆይበት ቦታ ሲያዘጋጅ ከእስር እንደሚወጣ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ያሲን ጁማ ከእስር እንዲለቀቅ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከያሲን ጁማ በተጨማሪ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአሥራት ሚዲያ ጋዜጠኞችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ከእነዚህም መካከል የኦኤምኤኑ ጋዜጠኛ መለሰም ከዚህ ቀደም የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት ከእስር እንዲወጣ ቢወስንም ፖሊስ በሌላ የወንጀል ድርጊት ጠርጥሬዋለሁ በማለቱ ከእስር ሳይለቀቅ ቀርቷል።
የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ደግሞ 'አመፅ ቀስቃሽ መልዕክት በጣቢያው ሲቀርብ ሠራተኞች ነበራችሁ' ተብለው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞቹ ሙሉጌታ አንበርብርና በላይ ማናዬ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያው ምስጋናው ከፈለኝ ሲሆኑ ከስምንት ወር በፊት የሚዲያ ተቋሙን የለቀቀው ዮናታን ሙሉጌታም እንደሚገኝበት ከጣቢያው መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ሽፈራው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።