ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴሌቪዥን የምንመለከትበትን ሰዓት መመጠን የከፉ የጤና ችግሮችን ይቀንሳል
በአንድ ቀን ከሁለት ሰዓታት በታች ቴሌቪዥን መመልከት ከአሳሳቢ የጤና ችግር እንደሚጠብቅ አንድ ጥናት ጠቁሟል።
የቴሌቪዥንና መሰል ስክሪኖችን አብዝቶ ከመመልከት ጋር ግንኙነት ያላቸው ካንሰር እና የልብ ሕመሞች በየቀኑ ከሁለት ሰዓታት ያልበለጠ ስክሪን በመመልከት ሊቀንሱ እንደሚችሉ ነው ጥናቱ የጠቆመው።
የግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የሠራው ይህ ጥናት ዕድሜያቸው ከ37 እስከ 73 ያሉ 500 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን በአውሮፓውያኑ ከ2006 እስከ 2018 ድረስ ቆይቷል።
የጥናቱ ውጤት እንደሚጠቁመው አዋቂዎች [ጎልማሳዎች] ከስክሪን ጋር ያላችውን ቁርኝት ሊቀንሱ ይገባል።
በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሁሉም ሰዎች በቀን ለሁለት ሰዓታት ብቻ ስክሪን ተመልክተው ቢሆን ኖሮ የመሞት እድላቸውን በ5.62 በመቶ ሊቀንሱ ይችሉ ነበር። ከልብ በሽታ ጋር የተገናኙ ሞቶች ደግሞ በ7.97 ሊቀንሱ ይችሉ ነበር ይላል ጥናቱ።
ጥናቱ ያካተተው ቴሌቪዥን መመልከት ብቻ ሳይሆን በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ቪድዮዎችን መመልከትንም ይጨምራል።
የግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የጤና ተቋም ባለሙያው ዶክተር ሃሚሽ ፎስተር ናቸው ጥናቱን የመሩት።
እሳቸው እንደሚሉት አብዝቶ ቴሌቪዥን መመልከትም ሆነ ከስክሪን ጋር ተጣብቆ መዋል ለጤና መቃወስ ያጋልጣል።
"ጥናታችን እንደሚጠቁመው ቴሌቪዥን አዘውትሮ አለመመልከት ለከፋ የጤና ችግር የመጋለጥ ዕድላችንን ከመቀነሱም በላይ ሊያዘገየው ይችላል።"
ዶክተሩ፤ በዘርፉ ላይ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያደርጉ ይጠቁማሉ።
አልፎም አብዝቶ ቴሌቪዥን መመልከት ማለት ቁጭ ብሎ የተለያዩ ምግቦችን ማጋበስ ስለሆነ ሌላ የጤና ቀውስ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።
ባለሙያዎቹ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ከመመልከት ይልቅ እንደ እርምጃ ያሉ ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዳበር ለጤናማ ሕይወት ጠቃሚ ነው ሲሉ ይመክራሉ።