ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ ኢትዮጵያን ማብራሪያ ጠየቀች
ግብጽ የኢትዮጵያ መንግሥትን በአስቸኳይ ስለ ግድቡ ውሃ ሙሌት ማብራሪያ እንዲሰጣት መጠየቋ ተሰማ።
ግብጽ ማወቅ የምትፈልገው ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ ሆን ብላ መሙላት መጀመር አለመጀመሯን ማወቅ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብጽ እያደረጉት የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር መቋረጡ እንደተሰማ ነበር የግድቡ ውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች መውጣት የጀመሩት።
ሱዳን በበኩሏ በታችኛው አገራት ያለው የውሃው ፍሰት በቀን 90 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትሮች መቀነሱን ገልፃለች።
ኢትዮጵያ ግድቡን በይፋ መሙላት አለመጀመሯን ተናግራለች።
5 ቢሊየን ዶላር የይፈጃል የተባለው ይህ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል ድርድር እየተደረገበት ቆይቷል።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማስታወቁን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የዘገቡ ቢሆንም በይፋ አለመጀመሩን ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ የግድቡ ሙሌት መጀመሩን አስመልክቶ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ዘገባው "በስህተት የወጣ ነው፤ የራስ ትርጉም ተጨምሮበታል። ግድቡ ግንባታው አሁን የደረሰበት ደርሷል፤ ግድቡ ውሃ ይይዛል እንጂ በይፋ የተጀመረ ነገር የለም" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስትሩ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት እነዚህ የሳተላይት ምስሎች የሚያሳዩት ከፍተኛ ዝናብ መኖሩንና ከግድቡ ከሚወጣው ይልቅ ግድቡ ውስጥ የሚገባው መጨመሩን ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዶ/ር ስለሺ ለቢቢሲ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት ውሃው ያልፍ የነበረው በ520 ከፍታ ላይ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 560 ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ከ560 ከፍታ በታች ያለው ውሃ ግድቡ ውስጥ የሚቀር እንደሆነና ሙሌቱም ከግንባታው ሂደት ጋር የማይነጣጠል ነው ማለታቸውንም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።