ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዋቂው ናይጄሪያዊ ሙዚቀኛ ደፍሮኛል ያለችው ሴት መታሰሯ ህጋዊነት የለውም ተባለ
ታዋቂው ናይጄሪያዊ ሙዚቀኛ ዲባንጂን ደፍሮኛል ያለችው ሴይታን ባባታዮ የተባለችው ሴት መታሰሯ ሕጋዊ አይደለም በማለት ጠበቆቿ ተቃወሙ።
ከሰሞኑ በቁጥጥር ስር የዋለችው ሴይታንንም አስመልክቶ ጠበቆቿ ለፖሊስ ይግባኝ ብለዋል።
ባለፈው ወር ነበር ሴይታን ሙዚቀኛው ኦላዳፖ ኦየባንጆ ወይም በቅፅል ስሙ ዲባንጂ ከሁለት ዓመት በፊት እንደደፈራት ያሳወቀችው።
የሙዚቀኛው ጠበቃ ማይክ ኦዜክሆሜ እንደገለፀው ደንበኛቸው እንዳልደፈራትና ክሱንም እንድትተው ደብዳቤ እንደጻፈላትና ይህንን ማድረግ ካልቻለች ግን ውንጀላ ነው በሚል ወደ ሕግ እንደሚወስዳት አመልክቷ ብለዋል።
በዚህ ሳምንትም ሴይታን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ የነበረ ሲሆን የተለቀቀችውም በዋስ እንደሆነ ተገልጿል።
ጠበቆቿ ሴይታን የታሰረችበትን ምክንያት እንዳላወቁና ሕጋዊነትም የለውም በሚል ቅሬታቸውን እንዳቀረቡ ጭምር አስታውቀዋል።
ከጠበቆቹ አንዱ የሆነው ቶሚ ኦጆጌ ዳንኤል እንደተናገረው ደንበኛው መደፈሯን ለፖሊስ ሪፖርት ያደረገቸው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው። የተደፈረችው ከሁለት ዓመት በፊት በዋና መዲናዋ ሌጎስ በሚገኝ ሆቴል መሆኑንም ተናግራለች።
ለምን ታሰረች ለሚለው ጥያቄ ቢቢሲ ለፖሊስ ቃለ አቀባዩ በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ አላገኘም።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በናይጄሪያ ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች ደፍረውናል የሚሉ ሪፖርቶች መበራከታቸውን ተከትሎም ከፍተኛ ተቃውሞዎች እየተደረጉ ነው።
የናይጄሪያ 36 ግዛት አስተዳዳሪዎችም ባለፈው ሳምንት ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ያስችል ዘንድ የድንገተኛ ህክምናና ጥሪ ማዕከል አቋቁመዋል።