ቻይና የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና መሥሪያ ቤትን በአዲስ አበባ ልትገነባ ነው

ቻይና የአፍሪካን የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል-ሲዲሲ ዋና መሥሪያ ቤትን በአዲስ አበባ እንደምትገነባ ፕሬዚዳንት ዢ ዢንፒንግ ተናገሩ።

የማዕከሉ ግንባታ ከታቀደው ጊዜ በፊት በዚህ ዓመት እንደሚጀመርም ፕሬዝደንቱ ጨምረው ተናግረዋል።

የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ዢንፒንግ ይህንን የተናገሩት ትናንት በቻይና-አፍሪካ ኮቪድ-19 ስብሰባ ላይ ሲሆን በጎርጎሳውያኑ 2020 መከፈል የነበረባቸው ከወለድ ነጻ ብድሮችን ለአፍሪካ አገራት እንደምትሰርዝም አስታውቀዋል።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ለተጎዱ የአፍሪካ አገራትም የብድር መክፈያ ጊዜ ይራዘምላቸዋል ብለዋል።

"የአፍሪካን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ፤ በአፍሪካ ኮቪድ-19ን ለመዋጋት ቻይና ከተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በጥምረት ተሰራለች" ሲሉ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል።

ዢ ዢንፒንግ ለቫይረሱ ክትባት ሲገኝ ከቻይና ሰራሹ ክትባት ቀድመው ተጠቃሚ የሚሆኑት አፍሪካውያን ናቸው ብለዋል።

ቻይና በመላው አፍሪካ የሆስፒታል ግንባታ ማድረግ እንደምትቀጥልም ፕሬዝደንቱ አስታውቀዋል። "በመላው አፍሪካ የቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት ሆስፒታሎች ግንባታ ይከሄዳል" ብለዋል ዢ ዢንፒንግ።

በዚህ ቻይና-አፍሪካ ኮቪድ-19 ሰብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ ማሃመት እና የበርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ተሳታፊ ነበሩ።