በህዳሴ ግድብ ድርድር በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት እንደተቻለ ተገለጸ

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ በሰነበተው ድርድር በበርካታ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መደረሱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስለድርድሩ ሂደት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው አብዛኞቹ ቴክኒካዊ ጉዳዮች በድርድሩ መፍትሄ እንዳገኙ የገለጸ ሲሆን ነገር ግን ለድርድሩ መቋጫ ለማበጀት ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ ገና መስማማት እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

ለዚህም የአገራቱ የቴክኒክና የሕግ ቡድን አባላት ከሚኒስትሮቹ ስብሰባ በፊት ተጓዳኝ ምክክር ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም ቡድን የደረሰበትን ውጤት ለሦስትዮሹ የሚኒስትሮች ስብሰባ ማቅረቡ ተነግሯል።

ባለፉት ሰባት ቀናት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ አሞላልና ዓመታዊ የውሃ ልቀት ላይ ታዛቢዎች ባሉበት በቪዲዮ ግንኙነት ድርድር ሲካሄድ ሰንብቶ በተለያዩ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውም ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ዘላቂ መብት ለማረጋገጥ የሚደረገው ድርድር ጥንቃቄን እንደሚፈልግ ገልጾ፤ ለዚህም ድርድሩ የግብጽና የሱዳን መንግሥታት የሁሉንም አገራት ሉአላዊነትና የጋራ ጥቅም ያከበረ አርቆ ለሚመለከት ዘላቂ ትብብር የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።

በድርድሩ ላይ ኢትዮጵያ የመርሆች ስምምነትን መሰረት አድርጋ ግድቡን በውሃ የመሙላትና ሥራውን የማካሄድ መብት እንዳላት ግልጽ ማድረጓን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

በዚህም ኢትዮጵያ ሦስቱም አገራት እያደረጉት ካለው በመመሪያዎችና ደንቦች ላይ እያካሄዱት ካለው ድርድር ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ስምምነት ላይ ተደርሶ እንዲጠናቀቅ ጽኑ ፍለጎት እንዳላት አመልክቷል።

በዚህ ሂደት የሱዳን ተደራዳሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ማነጋገር ስለፈለጉ ድርድሩ ለአንድ ቀን እንደተቋረጠ የተነገረ ሲሆን የሱዳኑ ውሃ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ማነጋገር ስለፈለጉ ድርድሩ በዛሬው እለት አይኖርም።

የሱዳን ተደራዳሪዎች ስለድርድሩ ሂደት ከጠቅላይ ሚኒስትራቸው ጋር ለመወያየትና መመሪያ ለመቀበል በመጠየቃቸው የትናንቱ ድርድር ከዚህ በኋላ እንዲካሄድ በመስማማት መጠናቀቁን ተገልጿል።

የሱዳን የሽግግር መንግሥት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌፍተናንት ጀኔራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።