በሶማሊያ በአውሮፕላን አደጋ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

ስድስት ሰዎችን ጭኖ ሲበር የነበረ አውሮፕላን በሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተነገረ።

አውሮፕላኑ ትናንት ከሰዓት ባርዳሌ በምትባል ከተማ በሚገኝ አየር ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር አደጋው እንዳጋጠመው ተገልጿል።

አውሮፕላኑ ንብረትነቱ የአፍሪካን ኤክስፕረስ ኤርዌይስ የተባለ የኬንያ አቪዬሽን ድርጅት እንደሆነና በወቅቱ የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች የሆኑ መድሃኒቶችንና የወባ መከላከያ ዛንዚራዎችን ጭኖ እንደነበር ተገልጿል።

የሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ምክትል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሃሳን ሁሴን ለቢቢሲ እንደገለጹት ከሟቾቹ መካከል አራቱ ሶማሊያውያን ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ኬንያውያን ናቸው።

ሚኒስትሩ አክለውም አውሮፕላኑ በምን ምክንያት እንደተከሰከሰ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነና ከዚህ የበለጠ ተጨማሪ መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

አፍሪካን ኤርዌይስ የኬንያ አቬዬሽን ኩባንያ ንብረት ሲሆን ከሶማሊያ መንገደኞችንና ቁሳቁስ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሲያመላልስ ቆይቷል።

አውሮፕላኑ የመድኃኒት እና የህክምና እቃዎችን ይዞ ከሞቃዲሹ ጌዶ ተብሎ ወደሚጠራ የሶማሊያ ግዛት እየበረረ እንደነበረ የሶማሊያ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አፍሪካን ኤርዌይስ እ.አ.አ. 1986 የተመሰረተ እና ከ30 በላይ መዳረሻቸዎች እንዳሉት ከአየር መንገዱ ድረ-ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ከአየር መንገዱ መዳረሻዎች በርካታዎቹ የሶማሊያ ከተሞች ናቸው።

አየር መንገዱ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የግል አየር መንድ ስለመሆኑ እና ዋና መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ስለማድረጉም በድረ-ገጹ ሰፍሯል።