ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የ99 ዓመቱ ሽማግሌ 4 ሚሊዮን ፓውንድ ሰበሰቡ
በዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛ ሁኔታ ምስጋና እየተቸራቸው የሚገኙት የጤና ባለሞያዎች ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ለነፍሳቸው ሳይሳሱ፣ ሕይወታቸው ለአደጋ እንደሚጋለጥ እያወቁ ይህ ኮሮና የሚባለውን የማይታየውን ባለጋራ ፊት ለፊት እየተጋፈጡት ያሉት የጤና ባለሞያዎች በመሆናቸው ነው።
እኚህ የ2ኛው ዓለም ጦርነት ጀግናና ባለሜዳይ እነዚህን የጤና ባለሞያዎችን ለማመስገን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ያምናሉ።
ከቤታቸው ጓሮ በሚገኝ ሜዳ 100 ዙር ለመሮጥና እና በዚያ መንገድ በሚገኝ ትኩረት ለጤና ባለሞያዎች የሚሆን የእርዳታ ገንዘብ ለማሰባሰብ አሰቡ።
መጀመርያ ሽማግሌው ለማሰባሰብ የፈለጉት 1ሺ የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ነበር። እርሳቸው በቢቢሲ ቴሌቪዥን ከቀረቡ በኋላ ግን የዓለምን ሕዝብ ከፍተኛ ትኩረት በማግኘታቸው ገንዘቡ ከሚሊዮን አልፏል።
ሽማግሌው አቶ ቶም ሙር ነው የሚባሉት፤ ሻምበል ናቸው። የሚኖሩት በቤድፎርድሻያር አካባቢ ነው። ባለፈው ሐሙስ መቶ ዙር እሮጣለሁ ብለው ተነስተው ለአዛውንቶች በተሰራ ድጋፍ ምርኩዝ ይህንኑ አሳክተዋል፤ እየተራመዱም ቢሆን።
በዚህ ያልረኩት ሽማግሌው ሌላ 100 ዙር ሩጫ አደርጋለሁ ብለዋል።
የብሔራዊ ጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ቻሪቲስ ቱጌዘር የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ሽማግሌው ያሰባሰቡት ገንዘብ ተቀብሎ ለሚመለከተው ያደርሳል።
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የሽማግሌውን በጎ ተግባር "አርአያነት ያለውና የሚያነቃቃ" ብሎታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 170ሺ ሰዎች በሽማግሌው ተግባር ልባቸው ተነክቶ ገንዘብ በኢንተርኔት ያዋጡ ሲሆን ይህ ዘገባ እስኪታተም ድረስም መጠኑ 4 ሚሊዮን የእንግሊዝ ስተርሊን ፓውንድ ደርሷል።
ሽማግሌው አቶ ሙር ይህን ሐሳብ ያመነጩት ኮሮናቫይረስን በመዋጋት ከፊት ለቆሙ የጤና ባለሞያዎች ምስጋና ለማቅረብ ነው።
አቶ ሙር ራሳቸው ኮሮናቫይረስ ባይዛቸውም በካንሰር ሕመም እና ዳሌያቸው አካባቢ ስብራት አጋጥሟቸው ሳለ የጤና ባለሞያዎች ስለረዷቸው ልባቸው ተነክቷል። ለጤና ባለሞያዎች ምስጋና የሚሆን ቃል የለኝም ይላሉ።
እነርሱን ለማመስገን ነው በቀን 100 ዙር ጓሯቸው አካባቢ 'የሚሮጡት'።
በሲቪል ምሕንድስና የሰለጠኑትና በ2ኛው የዓለም ጦርነት በህንድና በርማ የዘመቱት ካፒቴን ሙር ለ1ሺ ፓውንድ ጣሪያ የጀመሩት ገንዘብ የማሰባሰብ ሂደት አንድ ሚሊዮን ሲደርስ ልባቸው ተነክቶ እምባ ተናንቋቸው ነበር።
አቶ ሙር በዚህ ወር መጨረሻ መቶ ዓመታቸው ይደፍናሉ።