ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረው ምንድነው?
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ አንድ ወጣት ዛሬ ጠዋት በግቢው ውስጥ ድብደባ ደርሶበት ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል።
ተማሪው ወደ መመገቢያ አዳራሽ በሚሄድበት ወቅት ድብደባው እንደረሰበት ቢቢሲ ያነጋገረው ተማሪ ሰኢድ መሃመድ ገልጿል።
''ከጠዋቱ ሁለት ሰአት አካባቢ ወደ መመገቢያ አዳራሽ እየሄደ እያለ ሶስት የሚሆኑ ልጆች ተሰብስበው እንደደበደቡት ሰምቻለሁ'' ብሏል።
''ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ወደ ሆስፒታል ወስደነው ከረፋዱ አምስት ሰአት አካባቢ ነው ሕይወቱ ያለፈው። የልጁ ሞት ከተሰማ በኋላ በዩኒቨርሰቲው ብጥብጥ ተነስቶ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል" ሲልም ሰኢድ አክሏል።
በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሰይድ የሱፍ፤ ሁለት ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ነግረውናል።
''ሁለት ተማሪዎች ለህክምና ወደ ተቋማችን መጥተዋል። አንደኛው ህክምና እየተከታተለ ባለበት ወቅት ሕይወቱ ያለፈች ሲሆን ሌላኛው ተማሪ ግን ቀላል ጉዳት ስለደረሰበት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል'' ብለዋል።
ሕይወቱ ያለፈው ተማሪ ምን አይነት ጉዳት እንደደረሰበት ገና አልተጣራም ያሉት ሥራ አስኪያጁ ''እኛ የሠራነው የህክምና ባለሙያዎችን አስተባብረን ፈጣን ህክምና እንዲያገኝ ማድረጉ ላይ ነው። በወቅቱ ጽኑ ህሙማን ተኝተው የሚታከሙበት ክፍል ውስጥ ነው ሲታከም የነበረው'' ብለዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው፤ አንድ ተማሪ ሕይወቱ ማለፉን ያረጋገጡ ሲሆን ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መወሰዳቸውን ነግረውናል።
''በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ተማሪያችን ጉዳት ደርሶበት ሕይወቱ አልፏል። በግቢው ውስጥ በግንባታ ሥራ ላይ የነበረ አንድ ግለሰብም በግርግሩ ጉዳት ደርሶበታል። ሶስተኛው ጉዳት የደረሰበት ግጭቱን ለማብረድ መሀል የገባ የጥበቃ አባል ነው።''
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከቀናት በፊት ተማሪዎችን በማሰባሰብ ትልቅ የእርቅና የይቅርታ መድረክ አዘጋጅተው በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁንና የአሁኑ ክስተት ነገሮችን ወደኋላ የጎተተባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
''እርቅ ሁለት ጊዜ አድረገናል። እናቶችና አባቶች ከቀኑ ስድስት ሰአት እስከ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ተንበርክከው ተማሪዎችን አስታርቀዋል። የሀይማኖት አባቶች ጭምር መጥተው መልእክት አስተላልፈዋል።''
እሳቸው አንደሚሉት፤ ተማሪው ተላቅሶ እየተቃቀፈ እርቅ ከፈጠረ በኋላ አንዱ መጥቶ የሆነ ነገር ያደርግና ያ ሁሉ እርቅና ሰላም ተረስቶ ድፍርስርሱ ይወጣል። "ግቢያችንን ለመበጥበጥ አንድ ቀላል ነገር በቂ ነው። ጥፋተኛ ተማሪዎችን ማግኘት ከባድ ነው። የሆነ ነገር ያደርግና ከተማሪዎች ጋር ይቀላቀላል'' ሲሉም አስረድተዋል።
ከዛሬው ክስተት በኋላም ከምሥራቅ አማራ የፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር የማጣራትና የክትትል ሥራ እንደሚከናወን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
''የምሥራቅ አማራ የፌደራል ፖሊስ ዋና አዛዥ በተገኙበት ለተማሪዎች ትዕዛዝ ተላልፏል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ገብተውበታል የተባለው ህንጻ ላይ ተገቢውን ማጣራት አድርገን እርምጃ እንወስዳለን። ተማሪዎቹ እራሳቸው ካጋለጡ እሰየው፤ ካላጋለጡ ግን የራሳችንን አማራጭ እርምጃ እንወስዳለን።''
ተማሪ ሰኢድ እንደነገረን ከሆነ፤ ከተለያየ ብሔር የመጡ ተማሪዎች ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በተለያየ ማደሪያ ውስጥ እየኖሩ ነው።
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተም ጉዳዩ እውነት ነው ብለዋል።
''በአሁኑ ሰአት ምርጫ የለንም። ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ይሄን መሰል ችግር ሲፈጠር የነበረው። አንድ ዶርም ውስጥ የሚያድሩ ጓደኛማቾች እኮ እስከመገዳደል ደርሰዋል። ስለዚህ ተለያይተው እንዲኖሩ ማድረጋችን አማራጭ ስላጣን ነው። ለምሳሌ ዛሬ አንደኛውን ለብቻ ሌላኛውን ለብቻ በተለያየ ሰአት ነው ምግብ ያበላነው፤ በፌደራል ፖሊስም እንዲጠበቁ እያደረግን ነው'' ብለዋል።
ተማሪ ሰኢድ ''ሁሌም አለመረጋጋት ይፈጠራል፤ በነጋታው ትምህርት ጀምሩ እንባላለን። መንግሥትም ሆነ ዩኒቨርሲቲው መፍትሄ ሊሰጡን ይገባል። ወይም ደግሞ እንደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ወደቤታችን ይላኩን'' ይላል።
ዶ/ር አባተ ግን ተማሪዎችን ወደቤታቸው መላክ አማራጭ አያደለም ብለዋል።
''ተማሪዎችን ወደቤታቸው አንልክም፤ ተማሪውን አሳትፈን ለችግሮቹ መፍትሄ እንፈልጋለን እንጂ ወደቤት ልከን ለቤተሰቦቹ ሌላ ሸክም እንዲሆን አንሻም'' ሲሉም ያስረዳሉ።