ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መመሳሰላቸው እጅጉን የበዛ መንትዮች
የመንትዮች በተለይም ከአንድ የዘር እንቁላል የተፈጠሩ፤ በፆታም በመልክም ፍፁም አንድ ዓይነት የሆኑ መንትዮች በብዙ ነገር መመሳሰል የሚያስገርም አይደለም። የናይጄሪያዎቹ መንትዮች ፍሎረንስ ኦላዎይን እና ኢኑስ ኪሂንዴ አድሪናን መመሳሰል ግን ከተለመደው ውጭ እጅግ የበዛ ይመስላል።
የ55 ዓመቶቹ መንትዮች ያገቡት የወለዱትም በአንድ ቀን ነው። አንድ ላይ ሆነው ቤተ ክርስትያን አቋቁመዋል፤ እነሱም ባሎቻቸውም ፓስተሮች ናቸው።
መንትዮቹ እድሜያቸውን ሙሉ አብረው ነው የኖሩት። በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ምእራብ ናይጄሪያዋ አይባዳን ከተማ አንድ ግቢ ውስጥ ከየቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ ነው።
"ልጆች እያለን በተለይም በቤት ውስጥ ሥራ እንጣላ ነበር ግን ማንም፤ ወላጆቻችን እንኳ አያስታርቁንም ነበር። እራሳችን ነበርን የምንታረቀው" ትላለች ኦላዎይን።
በናይጄሪያ ዮሩባ ባህል መንትዮች ሁሉ በአንድ ዓይነት ስም ይሰየማሉ። ከማህፀን መጀመሪያ የወጣው 'ታይዮ' ሲባል ትርጓሜው የመጀመሪያ ማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ 'ኪህንዴ' ሁለተኛ ይባላል።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሳሉ በመተሳሰብ የአንዳቸውን ቅጣት ሌላኛቸው ተቀብለዋል። አስተማሪዎቻቸው ሳያውቁት አንዳቸው ለሌላኛቸው ፈተና ተፈትነዋል።
በእቅድ ይሁን ግጥምጥሞሽ ሁለቱም በአንድ ቀን በአንድ ሆስፒታል ወልደዋል። ልጆቻቸውን በአንድ ቀን አስጠምቀዋል። አንዳቸው እቤት ውስጥ ከሌሉ ቤት ያለ የሁለቱንም ህፃናት ልጆች ያጠባም ነበር።
ልጆቻቸው አሁን ትልልቅ ሲሆኑ በተለይም በስልክ እናቶቻቸውን በድምፅ መለየት እንደሚቸግራቸው ይናገራሉ።