ወንድማማቾች አግብተው የነበሩ ፓኪስታናውያን በጋራ ራሳቸውን አጠፉ

ፓኪስታን ውስጥ በጋራ ራሳቸውን ያጠፉ ሁለት ሴቶችን ጉዳይ ፖሊስ እየመረመረ ይገኛል።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ድህነት የተንሰራፋባት አካባቢ ራሳቸውን ያጠፉት ናታሁ ቤይ እና ቬሩ ቤይ ከወንድማማቾች ጋር ትዳር መስርተው ነበር።

ወንድማማቾቹ አርሶ አደሮች ሲሆኑ፤ የሟቾቹ አስክሬን የተገኘውም በሚኖሩበት የእርሻ መሬት ላይ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ወንድማማቾቹ እና ባለቤቶቻቸው የበቆሎ ምርት ለመሰብሰብ እርሻው አቅራቢያ እየኖሩ ነበር።

ሴቶቹ ለምን ራሳቸውን እንዳጠፉ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ በአካባቢው ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ይነገራል።

ታሀር የሚባለው አካባቢ በተፈጥሮ ኃብት የበለጸገ ቢሆንም፤ በፓኪስታን እጅግ ከደኸዩ ስፍራዎች አንዱ ነው። በአካባቢው ከህሪ በምትባለው መንደር ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ናታሁ እና ቬሩ ለምን ራሳቸውን እንዳጠፉ አለማወቁን ፖሊስ ገልጿል።

ካብር ካህን የተባሉ የፖሊስ ኃላፊ ወቅቱ ሰብል የሚሰበሰብበት በመሆኑ በረሀብ ምክንያት ራሳቸውን አጠፉ ማለት እንደማይቻል ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ከሥራ ጫና ወይም ቸል ከመባል ጋር የተያያዘ ሊሆንም ይችላል" ብለዋል።

አስክሬናቸውን የመረመሩት ዶ/ር ፑሻ ራሜሽ፤ ሰውነታቸው ላይ ጉዳት አለመኖሩን እና መላው ቤተሰባቸው በሀዘን መሰበሩን ገልጸዋል።

በሀያዎቹ መጀመሪያ ላይ ስለሚገኙት ናታሁ እና ቬሩ እምብዛም ባይታወቅም፤ ቬሩ የአንድ ዓመት ልጅ እንዳላት የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚኖር አላህ ጆዲዮ የተባለ ግለሰብ እንደሚለው፤ ሁለቱን ሴቶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ የሚያስገድድ ምክንያት ነበር ወይ? ሲል ባለቤቶቻቸውን እና አባታቸውን ጠይቆ፤ ምንም የተለየ ነገር አለመከሰቱን ነግረውታል።

ምናልባትም በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ያለ አለመግባባት ለሞት እንደዳረጋቸው አላህ ይጠረጥራል።

"ኑሯችን ከእጅ ወደ አፍ ነው። ላለፉት ወራት የእርሻ መሬቱ ላይ ሲሠሩ ስለነበር አለመግባባቶች ተፈጥረው ይሆናል። ወጣቶች ስለሆኑ በንዴት ተገፋፍተው፣ ባልበሰለ አዕምሮ የወሰኑት ውሳኔ ሊሆን ይችላል" ብሏል።

ዘንድሮ፤ ታሀር በሚባለው አካባቢ ቢያንስ 59 ሰዎች ራሳቸውን አጥፍተዋል። ከነዚህ 38ቱ ሴቶች፣ ሁለቱ ደግሞ ህጻናት ናቸው። በዚህ ስፍራ ባለፈው ዓመት 198 ሰዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን 'አዋሬ ዶት ኦርግ' የተሰኘ ድርጅት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ድርጅቱ ራስ ለማጥፋት ምክንያት ያለው ድህነትና በነዳጅ ቁፋሮ ፕሮጀክት ከቤት ንብረት መፈናቀልን ነው።

የመብት ተሟጋቾች በሠራተኞች መካከል የሚፈጠር እሰጣ ገባን እንደምክንያት ያስቀምጣሉ። መንግሥት አቅመ ደካሞችን የሚደጉምበት አሠራር አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰውም ይገልጻሉ።

ፓኪስታን ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ሙስሊሞች ሲሆኑ፤ በአካባቢው የሚኖሩት የተገለሉ ሂንዱዎች ናቸው። ከፍተኛ ቦታ የተሰጣቸው ሂንዱዎች እንዲሁም ሙስሊሙ ማኅበረሰብም ነዋሪዎቹን ያንቋሽሻቸዋል።