ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአጋላጩ መረጃ የቦይንግ ኦክስጅን አቅርቦት ላይ ጥያቄ አስነሳ
የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በጉዞ ላይ ሳለ አደጋ ቢደርስ ተጓዦች ኦክስጅን ላያገኙ እንደሚችሉ አንድ የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ አጋለጠ።
ጆን ባርኔት የተባለው ግለሰብ የሠራው ጥናት፤ አውሮፕላኑ ውስጥ በአደጋ ጊዜ ኦክስጅን የሚያሰራጨው መሣሪያ የተበላሸ ወይም የማይሠራ መሆኑን እንዳሳየው ይፋ አድርጓል።
በአንድ የቦይንግ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ሆን ተብሎ የማይሠሩ መሣሪያዎች እንደሚገጠሙም አጋላጩ ተናግሯል።
ቦይንግ የጆን ባርኔትን ክስ አጣጥሎ፤ ሁሉም አውሮፕላኖቹ በጥራት እንደተሠሩና በደህንነት ረገድም አስተማማኝ እንደሆኑ ገልጿል። የድርጅቱ የቀድሞ የጥራት ተቆጣጣሪ ኢንጂነር ጆን፤ በጤና እክል ምክንያት ቦይንግን እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስ ለ32 ዓመታት ሠርቷል።
ቦይንግ በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ከየአቅጣጫው ውርጅብኝ በዝቶበታል።
787 ድሪምላይነር በመላው ዓለም ረዥም ርቀት በመጓዝ የሚታወቅ አውሮፕላን ነው። ቦይንግ ለተለያዩ አየር መንገዶች ሸጦትም ትርፋማ ሆኗል።
ጆን እንደሚለው ግን አውሮፕላኑን ለማምረት ጥድፊያ ስለነበር ለጥራቱ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም። ቦይንግ በበኩሉ ይህ መረጃ ስህተት እንደሆነና ድርጅቱ ለጥራት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጿል።
አጋላጩ ጆን፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2016 ላይ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ አደጋ ሲከሰት ኦክስጅን የሚያሰራጨው መሣሪያው ላይ ችግር አስተውሏል። ይህ መሣሪያ በአግባቡ ካልሠራ፤ የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ሕይወት አደጋ ውስጥ ይወድቃል።
አውሮፕላኑ በ35,000 ጫማ ከፍታ እየበረረ ከሆነና የኦክስጅን ማሰራጫ መሣሪያው ካልሠራ፤ ተሳፋሪዎች በአንድ ደቂቃ ራሳቸውን ይስታሉ። በ40,000 ጫማ ከፍታ ደግሞ በ20 ሰከንድ ራሳቸውን ይስታሉ። ይህ ሞት ወይም የአዕምሮ ጉዳት ሊያስከትልም ይችላል።
ጆን 300 የኦክስጅን ማሰራጫዎች ላይ ምርመራ አድርጎ 75ቱ በተገቢው ሁኔታ እንደማይሠሩ ማረጋገጡን ይናገራል። ጉዳዩ በጥልቅ እንዲፈተሽ ለማድረግ ቢሞክርም የቦይንግ አመራሮች እንዳስቆሙትም አክሏል።
በ2017 ለአሜሪካው የበረራ ተቆጣጣሪ ኤፍኤኤ ችግሩን ቢያሳውቅም አንዳችም እርምጃ አልተወሰደም። ኤፍኤኤ እንደሚለው ከሆነ ግን በወቅቱ ቦይንግ ይህንን ጉዳይ እየፈተሸ መሆኑን ተናግሯል።
2017 ላይ ኦክስጅን በአግባቡ የማያስተላልፉ መሣሪያዎች ከአገልግሎት ውጪ መደረጋቸውን ቦይንግ ገልጿል። ከእያንዳንዱ ተሳፋሪ ወንበር በላይ የሚገኘው የኦክስጅን ማስተላለፊያ በተደጋጋሚ መሞከሩንም አክሏል።
ጆን ችግሮቹን ሲያጋልጥ፤ ቦይንግ በአንጻሩ የጆን ሙያዊ ታማኝነት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ በማድረጉ፤ ጆን ቦይንግ ላይ ክስ መስርቷል። ቦይንግ በበኩሉ ሠራተኞቹ ማንኛውንም አይነት አስተያየትና ቅሬታ ለድርጅቱ እንዲያሳውቁ እንደሚያበረታታ እንዲሁም አስፈላጊውን ምርመራ እንደሚያካሂድም ተናግሯል።
ቦይንግ ውስጥ ስላለው አሠራር ያጋለጠ ሠራተኛ ጆን ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አውሮፕላን መከስከሱን ተከትሎ አራት የቦይንግ ሠራተኞች (የቀድሞ ወይም አሁንም ያሉ) ለኤፍኤኤ ጥቆማ አድርሰዋል።
በቦይንግ 737 ማክስ ግንባታ ከተሳተፉ የቀድሞ ሠራተኞች አንዱ የሆነው አዳም ዲክሰን፤ ቦይንግ ውስጥ በፍጥነት በርካታ ምርቶች እንዲገባደዱ ጫና እንደሚደረግ ይናገራል። ይህንን ቅሬታ ጆንም ይጋራል።
ባለፈው ወር የዴሞክራቶች የኮንግረስ አባል አልቢኖ ሲረስ፤ ከ737 ማክስ ዋና ኃላፊዎች አንዱ የላኩትን ኢሜል በማጣቀስ፤ የቦይንግ ሠራተኞች ከመጠን በላይ እንሚሠሩ መናገራቸው ይታወሳል። ቤተሰባቸው በቦይንግ ሊሳፈሩ ሲሉ ጥርጣሬ እንደሚገባቸውም ተናገረው ነበር።
ቦይንግ አውሮፕላኖቹ አስተማማኝ እንደሆኑና ከኤፍኤኤ ጋር ሆኖ ጥልቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል። መስከረም ላይ አዳዲስ ለውጦች ማድረጉን እንዲሁም የምርትና የአገልግሎት አስተማማኝነት ክፍል ማቋቋሙንም ተናግሯል።