በግድያ የተጠረጠሩት 22 ኢንች በምትሰፋ ቀዳዳ ሾልከው አመለጡ

ፖሊስ በካሊፎርኒያ በአስደናቂ መልኩ ከእስር ቤት ያመለጡ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ምስል ይፋ አደረገ።

ሳንቶስ ሳሙኤል ፎንሴካ እና ጆናታን ሳላዛር የ21 እና የ20 ዓመት ወጣቶች ሲሆኑ በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኙ ነበር። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የእስር ክፍላቸውን ጣራ በመቦርቦር 22 ኢንች ስፋት ያለው ቀዳዳ ከፈጠሩ በኋላ ሾልከው አምልጠዋል።

"በግድያ የተጠረጠሩ ሰዎች ከእስር ቤት ውጪ መሆናቸው በጣም አሳዛኝ ነው" በማለት የአከባቢው ፖሊስ አዛዥ ጆናታን ቶርንበርግ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ባለሰልጣናት አደገኛ ናቸው፤ የጦር መሣሪያ ሳይታጠቁ አይቀርም የተባሉትን ሁለቱን ተጠርጣሪዎች ፍለጋ ላይ ይገኛሉ።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን ለጠቆመ 5ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከእስር ቤት ሊያመልጡ የቻሉት የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ሊመለከቷቸው በማይችሉበት የመጸዳጃ ክፍል ጣሪያ በኩል ነበር።

21 ኢንች ብቻ ስፋት ያለው ቀዳዳ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች ማሾለክ መቻሉን ፖሊስ ተናግሯል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከአንድ ዓመት በፊት ነበር በተለያዩ የግድያ ወንጀሎች ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ሳንቶስ ሳሙኤል ፎንሴካ ሁለት ሰዎችን በመግደል ተጠርጥሮ የታሰረ ሲሆን፤ ጆናታን ሳላዛር ደግሞ የ20 ዓመት ወጣትን ተኩሶ ገድሏል የሚል ክስ ነበር የቀረበበት ግለሰብ ነው።

ሁለቱም ተከሳሾች ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ እየተከራከሩ ነበር።