በዚምባብዌ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በ320 እጥፍ ጨመረ

በዚምብባዌ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በአማካኝ በ320 እጥፍ ጨምሯል።

በኢኮኖሚ ቀውስ እየታመሰች ባለችው ዚምባብዌ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በዚህ መጠን የጨመረው ኃገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጋጥማትን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ነው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ምርታማነት ለመጨመር እንደሚያስችልም ተገልጿል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚሰጠው ኩባንያ ጄኔረተሮችን ለማስነሳት ለሚያስፈልገው ናፍጣ ከፍተኛ ገንዘብ በማስፈለጉ ይህ ውሳኔ መተላለፉም ተነግሯል።

ከሁለት አመት በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን መገርሰሳቸውን ተከትሎ ዚምባብዌ በሃገሪቷ ታሪክ ክፉኛ በተባለው የኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጠች ነው።

ከሶስት ወር በፊት የጨመረው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ዚምባብዌውያንን አስቆጥቷል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ዜጎቿ በመሰረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ንረት በተቸገሩበት ሰዓት የታሪፉ መጠን የዚህን ያህል መሆኑ ተቀባይነት የለውም እያሉ ነው።

መንግሥት በበኩሉ በከፍተኛ ደረጃ የሚያጋጥመው የኃይል መቆራረጥ አንዳንድ ጊዜም በቀን ለአስራ ስምንት ሰአታት መቋረጡ፤ የተለያዩ ፋብሪካዎች፣ የማዕድን ማውጫዎች ላይና ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጥሯል።

ይህ የኃይል መቆራረጥ ኃገሪቷ ካጋጠማት ድርቅ ጋር ሲደመር እየተንገዳገደ ያለው የዚምባብዌን ኢኮኖሚ ወደ አዘቅት ሊከተው ይችላል የሚሉ ፍራቻዎችም አሉ።