የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ቤጂ ኬይድ ኢሴብሲ፣ በ92 ዓመታቸው አረፉ

በነጻ ምርጫ የተመረጡት የመጀመሪያው የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ቤጂ ኬይድ ኢሴብሲ በ92 ዓመታቸው ማረፋቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ኢሴብሲ የዓለማችን በእድሜ የገፉ በስልጣን ያሉ ፕሬዝዳንት ነበሩ። በምን ምክንያት እንደገቡ ባለስልጣናት ባይናገሩም ረቡዕ እለት ነበር ሆስፒታል የገቡት።

በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ ሃገራት ውስጥ ተቀስቅሶ የነበረውን የአረብ አብዮትን ተከትሎ ቱኒዚያ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 በተደረገው ነጻ ምርጫ ነበር ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት።

የዓለማችን ጎምቱ ፕሬዝዳንት ቱኒዚያዊው ቤጂ ኬይድ ኢሴብሲ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ባጋጠማቸው ከባድ የጤና ቀውስ ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸው ተሰምቶ ነበር።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ በመጪው ሕዳር ወር በሚካሄደው ፕዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ዳግመኛ ለመመረጥ እንደማይወዳደሩ አስታወቀው ነበር።

  • በ2014 ቱኒዚያ ባካሄደችው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተመርጠው ፕሬዝዳንት ሆኑ።
  • ከ2011 ሕዛባዊ አመፅ በኋላ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቱኒዚያን መርተዋል።
  • ከ1960 ጀምሮ በተለያዩ የሚኒስትርነት ቦታዎች ሀገራቸውን፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርና የሕዝብ እንራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በመሆን አገልግለዋል።

ቤጂ ኬይድ ኢሴብሲ ወደ ስልጣን የመጡት ኒዳ ቱውንስ (የቱኒዚያ ጥሪ) የተሰኘ እስላማዊ መንግሥትን የሚቃወም ፓርቲ መስርተው ነበር።