ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ ያለበትን ለጠቆመኝ 1 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች
አሜሪካ የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ ያለበትን ለጠቆመኝ ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ኦሳማ ቢን ላደን ከተገደለ በኋላ ልጁ ሃምዛ ቢን ላደን የአልቃይዳ ቁልፍ ሰው ሆኗል። በዚህ ዓመት የአባቱን ገዳዮች ለመበቀል በምስልና በድምጽ የተቀረጸ መልዕክት ለተከታዮቹ አስተላልፏል።
መስከረም 11፣ 2001 አሜሪካ፣ ኒው ዮርክ ውስጥ የአውሮፕላን ግጭት በመፍጠር ወደ 3000 የሚጠጉ ሰዎች በመግደል ተጠያቂ የሆነው ቢን ላደን፣ ከአደጋው ከአስር ዓመት በኋላ በ2011 ፓኪስታን ውስጥ በአሜሪካ ልዩ ሃይል መገደሉ ይታወሳል።
30 ዓመት እንደሚሆነው የሚነገርለት ልጁ ሃምዛ ቢን ላደን፣ ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ መንግስት ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጇል።
መረጃው እንደሚያትተው ቢን ላደን የተገደሉት ልጃቸው ሃምዛን እየሞሸሩ በነበረበት ወቅት ነው። ቢን ላደን ልጁ ሀምዛ እንዲተካው የመጀመሪያ ምርው ነበር።
ሃምዛ በአፍጋኒስታንና በፓኪሰታን ድንበር አካባቢ ወይም ደግሞ ወደ ኢራን ተሻገሮ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
የት ቦታ እንዳለ በትክክል ባይታወቅም ደቡብ ማዕከላዊ እስያ ውስጥ ይገኛል ተብሏል። ስለዚህም አሜሪካ ያለበትን ትክክለኛ ቦታ ለሚናገር ሰው 1 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብላለች።