ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያው ሰላይ ነርቭን በሚጎዳ መርዝ የመግደል ሙከራ ደረሰበት
የቀድሞው የሩሲያ ሰላይ እና ልጁን ለመግደል ነርቭን የሚጎዳ መርዝ መጠቀማቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
እሁድ ዕለት ከሰዓት ሰርጌ እና ዩሊ ስክሪፓል እራሳቸውን ስተው የተገኙ ሲሆን አሁንም በፅኑ እንደታመሙ ናቸው።
በስፍራው ቀድሞ የደረሰው የፖሊስ አባልም በጠና ታሞ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እያገኘ መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ማርክ ሮውሊ ተናግረዋል።
ነርቭን የሚጎዱ ኬሚካሎች የነርቭ ሥርዓትን በማስተጓጎል የአካል እንቅስቃሴ እንዲገታ ያደርጋሉ።
ይህ መርዝ በአብዛኛው ወደ ሰውነት የሚገባው በአፍ ወይም በአፍንጫ ሲሆን በዓይን እና በቆዳም ሊገቡ ይችላሉ።
የፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ኃላፊ የሆኑት ሮውሌ እንዳሉት የመንግሥት ተመራማሪዎች የመርዙን ዓይነት የለዩት ሲሆን በዚህ ደረጃ መረጃውን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አልፈለጉም።
"ይህ እንደ ከባድ የመግደል ሙከራ ወንጀል ነው የተያዘው" ብለዋል።
"የሕመማቸው ምልክት ነርቭን የሚጎዳ ኬሚካል መሆኑን ከለየን በኋላ ሁለቱ ሰዎች ብቻ ተነጥለው ጥቃት እንደደረሰባቸው ማረጋገጥ ችለናል" ሲሉም አክለዋል።
ሌሎች የሕብረተሰቦችን ክፍል የሚያሰጋ የጤና አደጋ ግን አለመኖሩን አሳውቀዋል።
ሌሎች በስፍራው የነበሩ ሁለት የፖሊስ አባላት ለቀላል ጉዳት ሕክምና መከታተላቸውንም ጨምረው አብራርተዋል።