ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በካሌ ስደተኞች ጣቢያ በተነሳ ግጭት ኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳት ደረሰባቸው
በፈረንሳይ የወደብ ከተማ ካሌ በአፍጋናውያንና ኤርትራውያን በተነሳ ግጭት አምስት ስደተኞች ቆሰሉ።
እድሜያቸው ከ16-18 የሚሆኑ አራት ኤርትራውያንም አቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደው ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ሲሆን በአስጊ ሁኔታም ላይ እንደሚገኙ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
አምስተኛው ሰው ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ወደ ሌላ ከተማም ተወስዷል።
በግጭቱ 13 ሰዎች በብረት ዱላ በመደብደባቸውም እንደቆሰሉ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀራርድ ኮሎምብ አካባቢወንም ከጎበኙ በኋላ ከሌላው በተለየ መልኩ አደገኛ ሁኔታ ነው ያለው በማለት ገልፀዋል።
አንደኛው በጣም የተጎዳው ሰው አንገቱ ጀርባ በጥይት እንደተመታም ተገልጿል።
"ለካሌ ነዋሪዎችም ሆነ ለስደተኞቹ መቋቋም የማይችሉዋቸው ግጭቶች እየበረቱ ነው" በማለት ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የመጀመሪያው ግጭት ለሁለት ሰዓታት ያህል የቆየ ሲሆን ስደተኞቹም ለምግብ ተሰልፈው በነበረበት ወቅት ነው ግጭቱም የተነሳው።
በዚህ ግጭት ቁጥራቸው 100 የሚሆኑ ኤርትራውያንና 30 የአፍጋን ዜጎችም ተሳታፊ ነበሩ።
ግጭቱም የተነሳው አንድ የአፍጋን ዜጋ ሽጉጥ በመተኮሱ መሆኑን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።
"በኤርትራውያን የተከበቡትን የአፍጋኒስታን ዜጎችን ለማዳን ፖሊስ አካባቢውን ከቦት እንደነበርም" የአካባቢው አይን እማኝ ገልጿል።
የፈረንሳይ የፀጥታ ኃይልም ወደ አካባቢው ተልከዋል።
የካሌይ የስደተኞች መቆያ ወይም በቅፅል ስሙ ጫካው ተብሎ የሚታወቀው ይህ ቦታ ከሁለት አመት በፊት የፈረሰ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ወደ እንግሊዝ ማቋረጥ በሚያስቡ ከመቶዎች በላይ ስደተኞች መኖሪያ ነው።
የቀሩት ብዙዎቹም ወንዶች ናቸው።
በአካባቢው ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች የካሌ ስደተኞችን 800 ሲያደርሱዋቸው ባለስልጣናቱ ከ550-600 እንደሚደርሱ ገልፀዋል።