ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊቢያ ውስጥ 27 ሰዎች በቦምብ ጥቃት ተገደሉ
በሊቢያዋ ሁለተኛ ከተማ ቤንጋዚ ውስጥ በሚገኝ አንድ መስኪድ አቅራቢያ ትናንት ምሽት በሁለት መኪኖች ላይ የተጠመዱ ቦንቦች ፈንድተው ቢያንስ 27 ሰዎች ተገደሉ።
በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ በፈነዱት ቦምቦች ምክንያት ከ20 እስከ 30 ተጨማሪ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል።
የመጀመሪያው ቦምብ የፈነዳው አል-ስሌይማኒ በተባለው ሰፈር ውስጥ ከሚገኝ መስኪድ ፊት ለፊት ሲሆን በወቅቱም ሰዎች የምሽት የፀሎት ፈጽመው ከመስኪዱ በመውጣት ላይ ሳሉ ነበር።
ሁለተኛው ቦምብ ደግሞ ከመንገድ በተቃራኒ ስፍራ ላይ የመጀመያውን ተከትሎ ነበር የፈነዳው።
ከቦምብ ጥቃቱ ሰለባዎች መካከል ሰላማዊ ሰዎችና ወታደሮች ይገኙበታል። በከተማው የሚገኘው የአል-ጃላል ሆስፒታል ቃል-አቀባይ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት የጥቃቱ ሰለባዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚል ተናግረዋል።
እስካሁን ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ ግልፅ አይደለም። የቢቢሲ የሰሜን አፍሪካ ዘጋቢ ራና ጃዋድ ማን እንደፈፀማቸው የማይታወቁ በርካታ ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃቶች ሊቢያ ውስጥ ከዚህ በፊት ማጋጠማቸውን ተናግራለች።
ከሰባት ዓመት በፊት ሙአማር ጋዳፊ ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ ሊቢያ ከባድ ጦርነት ውስጥ ወድቃለች። ሃገሪቱ ውስጥ ባሉት ሁለት ተቀናቃኝ ፓርላማዎችና ጠንካራ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የበላይነትን ለመያዝ በሚደረገው ፍልሚያ ምክንያት እስላማዊ መንግሥት የተባለው አክራሪ ቡድን ለመጠናከር እድልን አግኝቷል።
የቤንጋዚ ከተማ በወታደራዊው መስክ ሃያል በሆነው ሃሊፋ ሃፍታር በሚመራው፤ እራሱን የሊቢያ ብሄራዊ ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድንና እስላማዊ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች ሲካሄዱባት ቆይታለች።
ለሦስት ዓመታት ከተደረገ ፍልሚያ በኋላ ሃፍታር ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የቤንጋዚ ከተማን ሙሉ ለሙሉ ከእስላማዊ ታጣቂዎች ነፃ ማውጣቱን አሳውቆ ነበር።
ቢሆንም ግን በቤንጋዚ ከተማ ውስጥ የሚያጋጥሙት ግጭቶችና ጥቃቶች ቀጥለዋል።