ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምድር ሽንቁር ውስጥ የሚገኘው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ክምችት በታሪክ እጅግ ልቆ ተገኘ
የ2016 አሃዝ ከዚያ በፊት ከታዩ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ክምችቶች በ50 በመቶ የላቀና በ8 ሺህ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ያልታየ ነው ተብሏል።
አጥኚዎች እንደሚሉት ሰው ሠራሽ እና እንደ ኤልኒኖ የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ለካርቦንዳይኦክሳይድ መጨመር ምክንያቶች ናቸው።
ዓለም አቀፉ የሜትዮሮሎጂ ድርጅት የካርቦንዳይ ኦክሳይድ፤ ሚቴን እንዲሁም ኒትርየስ ኦክሳይድን ልቀት አካቶ ጥናቱን በ51 የዓለማችን ሃገራት ነው ያከናወነው።
ዓለም አቀፉ የሜትዮሮሎጂ ድርጅት አባል የሆኑት ዶ/ር ኦክሳና ታራሶቫ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅቱ መሰል ጥናቶች ማካሄድ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የአሁኑ አሃዝ እጅግ ከፍተኛው ነው።
ቀደም ያለው ከፍተኛው በምድር ከባቢ ሽፋን ሽንቁር ውስጥ የሚገኝ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ክምችት የተመዘገበው በ1997ቱ የኤልኒኖ ክስተት ወቅት ነበር።
የአሁኑ ግን ባለፉት አስር ዓመታት ከተመዘገበው በ50 በመቶ ልቆ ተገኝቷል።
በጥናቱ መሠረት መሰል የካርቦን ዳይኦክሳይድ ክምችት መጨመር ድንገተኛና አስከፊ ለሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች አጋላጭ ነው።
በዘርፉ ብዙ ልምድ ያላቸው ሰዎች የጥናቱ ውጤት ለምድራችን መፃኢ ዕጣ ፈንታ እጅግ አስጊ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጥሮ ጥበቃ ሃላፊ ኤሪክ ሶልሄይም "ቁጥሮች አይዋሹም። ይህንን አደጋ ለመመከት ብዙ መፍትሄዎች በእጃችን አሉ። የሚያስፈልገን ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።