ስለ ቭላድሚር ፑቲን ምን ያህል ያውቃሉ?

ፕሬዚደንት ቪላድሚር ፑቲን

እ.አ.አ. በ2000 ዓ.ም. የሩስያ ፕሬዚደንት ሆነው ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ቪላድሚር ፑቲን በሀገሪቱ እንዲሁም በዓለም ፖለቲካ ዑደት ላይ የጎላ አሻራ ማሳረፍ ችለዋል።

ፑቲን እንደ ምልክት ከሚታዩት ዲሚትሪ ሜድቬድቭ ስልጣን በድጋሚ ከወሰዱ በኋላ የሀገሪቱን መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ አዋሉ። የተቃዋሚ ወገኖች ሀይልም እየተዳከመ መምጣት ጀመረ። ብሔርተኝነት በሩስያ በሀይለኛው መሰበክ ያዘ። የምዕራቡን ዓለም የሚያጥላሉ መልዕክቶችም መደመጥ ጀመሩ።

በተለይ ደግሞ እ.አ.አ. በ2014 በሩስያ የሚደገፈው የዩክሬን መንግስት በአውሮጳ መንግስታት በሚደገፈው ተቃዋሚ ሀይል ከተናጠ በኋላ ፑቲን ያሳዩት መረር ያለ ምላሽ ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር።

ሩስያ ክሬሚያን ከዩክሬን ከወሰደች በኋላ የፑቲን ተቀባይነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየወረደ መምጣት ጀመረ። በምስራቃዊው የሩስያ ክፍልም አመፅ መቀስቀስ ጀመረ።

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የፑቲን ወዳጅ የሆኑተ የሶሪያው ባሽር አል-ኣሳድን በመደገፍ እንዲሁም በሶሪያ የሚገኘው የሜዲቴራኒያን ባህር ሀይላቸውን ለመከላከል በሚል አየር ሀይላቸው የሶሪያ ሽምቅ ተዋጊዎችን እንዲያጋይ ላኩ።

ፑቲን ራሳቸውን ሩስያን ከ1990ዎቹ ምጣኔ ሀብታዊ፥ ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውስ በማውጣት ለዚህ ያበቃሁ ነኝ በማለት ያሞካሻሉ። በማከልም የሩስያን ፍላጎት በማስጠበቅ ከምዕራባዊያን ጫና ያላቀቅኩ ጠንካራ መሪ ነኝ ሲሉም ይደመጣሉ።

በዚህ በኩል ደግሞ ተቺዎቻቸው ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ከፊውዳሊዝም ያልተናነሰ ስርዓት በመግንባት ገበያውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዳይመጣ መንገዱን ዘግተዋል በማለት ይወቅሷቸዋል።

ፑቲን የሚቃወሙ በርካቶች መጨረሻቸው ስደት እና እስራት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ተቃዋሚው ሚክሄይል ኮዶርኮቭስኪ ግብር አጭበርብሯል በሚል በ2003 ዓ.ም. ለአስር ዓመታት ወደ እስር የተላከበት መንገድ ማሳያ ነው።

ኬጂቢ

እ.አ.አ. በ1952 በቅዱስ ፒተርስበርግ የተወለዱት ቪላድሚር ፑቲን የሩስያውን የስለላ መረብ ኬጂቢን የተቀላቀሉት በሶብየት ህብረት ፖሊስ መልክ ነበር። ከ1996 ወደ ሞስኮ ከመዛወራቸው በፊት በቅዱስ ፒተርስበርግ አመራር ውስጥ ይሰሩ ነበር። ነሃሴ 1999 ላይ ፑቲን ጠቅላይ ሚንስትር ሆኑ።

ተጠባባቂ ፕሬዚደንት ከሳቸው በፊት በነበሩት ቦሪስ የልሲን ተሾሙ። በወርሃ ግንቦት 2000 ዓ.ም. ፕሬዝደንታዊ ምርጫውን በማሸነፍ የሀገሪቱ መራሄ መንግስትን መንበር ተቆጣጠሩ። በተለይ ደግሞ በቼቼን አማፅያን ላይ ባካሄዱት የተሳካ መልሶ የማቃት እርምጃ ፑቲን የሩስያውያን ልብ ውስጥ መግባት ጀመሩ። በ2004 ዓ.ም እንደገና ፕሬዚደንታዊ ምርጫውን ማሸነፍ ቻሉ።

ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት ለፕሬዚደንትነት መወዳዳር የሚከልከለውን የሩስያ ህገ-መንግስት በመከተል በ2008 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚንስትራቸው ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በመተካት ከአራት ዓመታት በኋላ እንደገና በ2012 መንበረ ፕሬዚድነቱን ተቆጣጠሩት።

አሁን ላይ የሩስያ ፓርላማ የአንድ መሪን ቆይታ ከአራት ወደ ስድስት ዓመት አራዝሞታል። ብዙ ዓመት ካገለገሉ የአውሮጳ መሪያት አንዱ የሆኑት ፑቲንም በ2018 እንደገና መመረጥ ከቻሉ እስከ 2024 ዓ.ም ድረስ መምራት ይችላሉ ማለት ነው።