ለ25 ዓመታት ተግባራዊ ያልሆነው የኤርትራ ሕገ መንግሥት

በኤርትራ ውስጥ ለ30 ዓመታት የተካሄደው እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግል በመጨረሻም በአውሮፓውያኑ ግንቦት 1991 የደርግን መንግሥት በማሸነፍ ተደመደመ።

ወታደራዊ ድሉ ከተገኘ ከሁለት ዓመት በኋላ ኤርትራን ሃገር ሆና እንድትመሰረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባልም እንድትሆን በተደረገው ህዝበ ውሳኔ 99.8 በመቶ ህዝቧ ድጋፉን ሰጠ።

አገሪቱ ሰፊ በሆነ የህዝብ ተሳትፎ በተደገፈ የሦስት ዓመታት ዘመቻ ከተካሄደም በኋላ በአውሮፓውያኑ ግንቦት 23 ቀን 1997 ህገ መንግሥቷን በይፋ አጽድቃለች።

ነገር ግን የጸደቀው ህገ መንግሥት ከሩብ ምዕተ አመት በኋላም በፕሬዚዳንቱ መሳቢያ ውስጥ ተቆልፎበት ይገኛል ።

በመቀጠልም ብሔራዊ ምርጫዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘሙ እንዲሁም የህግ የበላይነት እና ፍትህ ተረገጠ።

ከዚህም ባለፈ ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በተለያዩ የሰብዓዊ ተሟጋች ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ በማድረስ የምትወቀስ ሃገር ከመሆን አልፋ በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ቀያቸውን ጥለው ከሃገር መሰደዳቸውን ቀጥለዋል።

ኤርትራ የነፃነት ቀኗን በምታከብርበት በዚህ ወር ቢቢሲ ትግርኛ ህገ መንግሥቱ ከመጠንሰሱ ጀምሮ አዘገጃጀቱን በተመለከተ የየህገ መንግሥቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር የነበሩትን ዶ/ር በረከት ሃብተ ሥላሴን እንዲሁም የኮሚሽኑ የቀድሞ አባላትን በላይነሽ አርአያ እና ጳውሎስ ተስፋጊዮርጊስን አነጋግሯቸዋል።

በኤርትራ የተካሄደው የረዥም ጊዜ የትጥቅ ትግል ዓላማ ሕገ መንግሥታዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመዘርጋት ነበር።

በህዝበ ውሳኔው የተገኘውን ደስታ ህዝቡ ካጣጣመ በኋላ አገራዊ ትኩረቱ ወደ ብሔራዊ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሄደ።

የሕገ መንግሥት ኮሚሽኑን እንደሚመሩም ዶክተር በረከት ሀብተሥላሴ ተመረጡ። ዶክተር በረከት ኮሚሽኑን በኃላፊነት እንዲመሩ የተመረጡበት በሁለት ምክንያቶች ሲሆን በመጀመሪያ ሕገ መንግሥታዊና ሕግ ዋነኛ የሙያ ዘርፋቸው ስለሆነና ጥልቅ ዕውቀት ስለነበራቸው ነው።

በሁለተኛነት ደግሞ አሥመራን ነጻ በማውጣት ከፍተኛ ስፍራ ያለው ሻዕቢያ (የኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅት) ጋር ከነበራቸው ግንኙነት ጋር ተያይዞ ነው።

በአውሮፓያኑ 1993 ዶ/ር በረከት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በወቅቱ የአሜሪካ መልዕክተኛ በነበሩት በሃጎስ ገብረህይወት አማካኝነት በቴሌክስ መልዕክት ደረሳቸው።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የላኩት መልዕክት ዶ/ር በረከት የሕገ መንግሥት ኮሚሽኑን እንዲመሩ የሚጠይቅ ነበር።

ነገር ግን ዶ/ር በረከት በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሻዕቢያን በርካታ ስራዎች ሲያከናውኑ ከቤተሰቦቻቸው በመራቃቸው ምክንያት በቤተሰብ ጉዳይ ጥያቄውን እንደማይቀበሉት አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ ግን በጥያቄያቸው ገፉበት። ጓደኞቻቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸውም እንዲሁ ኮሚሽኑን በኃላፊነት የመምራቱን ኃላፊነት እንዲቀበሉ ተማጸኗቸው ። ዶ/ር በረከት ወደ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ በነበራቸው ጉዞም ወደ አሥመራ በማቅናት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ስለዚሁም ጉዳይ ተወያይተዋል።

በዚህም ውይይት ኮሚሽኑን በመምራት ረገድ ስለተሰማቸው የሞራል ግዴታ እና ጫና እንዲሁም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለጥረታቸው የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም የገቡትን ቃልም አንስተዋል።

የኤርትራ ሕገ መንግሥት ኮሚሽን ምስረታ

የኤርትራ ፓርላማ በአዋጅ 37/1993 ለዴሞክራሲ ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም የሕገ መንግሥት ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 55/1994 ተቋቋመ። ምስረታውም በአገር ውስጥ ጋዜጦች ታተመ። ኮሚሽኑ ሃምሳ አባላት ያሉት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ ሴቶች ናቸው።

ሚያዝያ 1994 ኮሚሽኑ የኤርትራ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ በይፋ መጀመሩን ለማወጅ በአሥመራ ሲምፖዚየም አካሄደ።

በሲምፖዚየሙ ላይ ምሁራን ፣የውጭ ባለሙያዎች፣ የውጭ ኤምባሲ ተወካዮች ተሳትፈዋል። በዚያን ወቅትም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሕገ መንግሥት ስለመኖሩ አስፈላጊነት ረዥም ንግግር አድርገዋል።

የሕገ መንግሥቱን የማርቀቅ ሂደት አስፈላጊነት ለማጠናከር እና የህዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ በኤርትራ ውስጥ እና በውጭ አገራት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል።

የአካባቢው እና የሸሪዓ ህጎች ጥናት፣ የሌሎችን አገሮች ልምዶች መፈተሽ እንዲሁም በተለያዩ የአስተዳደር ስርዓቶች መካከል ያለውን ልዩነት ለማየት ጉባኤዎች ተካሄዱ።

የኮሚሽኑ አባል የሆኑት አቶ በላይነህ አርዓያ እንደሚሉት "ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱን ካረቀቀ በኋላ ረቂቁን ለተጨማሪ ውይይት ወደ ህዝቡ ወስዶታል። በመጨረሻም የኤርትራ ሕገ መንግሥት ግንቦት 23 ቀን 1997 በፓርላማ ጸደቀ"

ለ25 ዓመታት ተግባራዊ ያልሆነው ሕገ መንግሥት

የኤርትራ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን በድንገት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል በአውሮፓውያኑ 1998 ሰኔ ወር ላይ የድንበር ጦርነት ተከፈተ።

ደም አፋሳሹ ጦርነት ለሁለት አመታት እስከ 2000 ድረስም ዘልቋል።

"አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ኤርትራ ግጭቱን በውይይት ለመፍታት የቀረበውን የሩዋንዳና የአሜሪካ የሰላም ጥያቄን መቀበል አለባት የሚል አመለካከት ነበራቸው። እንደ አለመታደል ሆኖ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አደረጉት" ሲሉ የቀድሞ የሕገ መንግሥት ኮሚሽን አባል ጳውሎስ ተስፋጊዮርጊስ ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የህዝብ መፈናቀልን አስከተለ።

አንዳንድ የኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግጭቱን በአግባቡ አልያዙም ሲሉ መተቸታቸውን ተከትሎ በመካከላቸው ግጭት ተፈጠረ።

ግጭቱም በኤርትራና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል በተደረገው የመጨረሻ እና አስገዳጅ የሰላም ስምምነት በአልጀርስ ስምምነት ተቋጨ።

ሁለቱ ሃገራት ስምምነቱን ታህሳስ 12፣ 2000 በአልጄሪያዋ መዲና አልጀርስ የፈረሙ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ሃይል በድንበር ላይ እንዲሰማራ ሆነ።

ሚኒስትሮች እና ጄኔራሎችን ጨምሮ አንዳንድ ለውጥ ፈላጊ የመንግሥት ባለስልጣናት ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ መደረግ አለበት ሲሉ ጠየቁ። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው ለዚህም ምላሻቸው እንዲህ አይነት ጥሪ ለማድረግ ትክክለኛው ወቅት አይደለም አሉ።

ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ አንጃዎች በፕሬዚዳንቱና የኤርትራው ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ (ህግደፍ) ግብረ አበሮቻቸው እና በተሃድሶ አራማጆች መካከል አለመግባባቱ እየሰፋ ሄደ።

ጂ-15 እየተባለ የሚጠራው 15 የተሃድሶ ፈላጊ ቡድን ፕሬዚዳንቱ የማዕከላዊ ኮሚቴውን እና የብሔራዊ ምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ አልጠሩም ሲሉ ከሰሷቸው።

ቡድኑ በተጨማሪም ለህግደፍና እና ለህዝቡ የጻፏቸውን ግልጽ ደብዳቤዎች ለህዝብ ይፋ አደረጉ። ብዙም ሳይቆይ ለአገር ውስጥ ጋዜጦች ቃለ መጠይቅ መስጠት ጀመሩ። አለመግባባቱም እየተካረረ መጣ።

"እንደ አለመታደል ሆኖ በአንድ ወቅት የተከበሩ የነጻነት ታጋይ የነበሩት ኢሳያስ አፈወርቂ ትልቁን ገጽታ ማየት አልቻሉም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኤርትራ በራዕይ ማነስ እና ይሄም ሁኔታ ባስከተለው ውድቀት ምክንያት ቁልቁል መንሸራተት ጀመረች " ይላሉ ዶ/ር በረከት። የሚጠበቀው ነገር ፈጽሞ እንዳልተሟላም አክለዋል።

ከፕሬዝዳንቱ ጋር በመሆን ለሶስት አስርት ዓመታት ሲታገሉ የነበሩና ሕገ መንግሥቱ ይከበር ብሎ ሲጠይቅ የነበረው ቡድን እንዲሁም የለውጥን አስፈላጊነት ሲዘግቡ የነበሩ የፕሬስ አባላትን በሙሉ እስር ቤት መታጎራቸው ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው በላይነሽ ያስረዳሉ።

የታጡ ዕድሎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ኤርትራ አራት ምርጫዎችን ታካሂድ እንደነበርም ያስረዳሉ ።

"መሰረታዊ የሆኑ ህገ መንግሥቱን ብትከተል ኖር ኤርትራ ከሚሰደደው ወጣቷ ጥፋት ልትድን ትችል ነበር። ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም መኖር እንዲሁም ልትበለጽግም ትችል ነበር" ሲሉ አክለዋል።

ስለ ሕገ መንግሥቱ የኤርትራ መንግሥት አመለካከት

የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ እና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት በሕገ መንግሥቱ መርህና መንፈስ እንደሚመሩ ነው የሚናገሩት።

ለምሳሌም ያህል በአውሮፓውያኑ 2013 በአትላንታ በተካሄደ ፌስቲቫል ላይ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ የማነ ሕገ መንግሥቱ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን በተጠየቁበት ወቅት ኤርትራ የምትመራው በብሔራዊ ሕገ መንግሥቱ መንፈስና ባሕርይ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አገራዊ ምርጫ የሚካሄደው ሁኔታዎች ሲረጋጉ እንደሆነም አክለዋል።

እውነት ነው በመንግሥት ባለስልጣናት የተሰጠውን ማብራሪያ ያመኑ በርካታ ኤርትራውያን ሕገ መንግሥቱ አንድ ቀን ተግባራዊ ይሆናል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

ነገር ግን ጊዜው እየጨመረ ሲመጣ ሕገ መንግሥቱ ሲተገበር የማየት ተስፋም እየደበዘዘና እየተሟጠጠ መጣ።

በጥር 2013 በኮሎኔል አሊ ሂጃይ የሚመራ "ፎርቶ አመፅ" የተሰኘ አመፅ በኤርትራ መንግሥት ላይ ተነሳ።

ኮሎኔሉ እና ደጋፊዎቻቸው ሕገ መንግሥቱ ስራ ላይ እንዲውል እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ጠየቁ። የአማፂያኑ መሪ በመንግሥት ወታደሮች ሲከበብም ራሱን አጠፋ።

ከዚህ ተቃውሞ በፊትም ሆነ በኋላ በርካታ በዲያስፖራ የሚኖሩ ኤርትራውያን የመንግሥትን አካሄድ በመቃወም ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ እንዲደረግና እስረኞች እንዲፈቱ የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።

ለዚህ ሁሉ የፕሬዚዳንቱ ምላሽ ምንድን ነው?

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአንድ ወቅት ኤርትራ ውስጥ መቼ ብሔራዊ ምርጫ ይካሄዳል? ተብለው በአልጀዚራ ሲጠየቁ ምላሻቸውን የሰጡት ቆጣ ባለ መልኩ ነበር። በንዴትም "ምናልባት ከ30-40 ዓመታት በኋላ ወይም ከዚያ በላይ" ብለው የመለሱ ሲሆን ይህም ምላሻቸው ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ያመላከተ ነበር።

"ፕሬዚዳንቱ በፈጸሟቸው ተደጋጋሚ ስህተቶች፣ ፍርድ ቤት ሊያቆሟቸው በሚችሉ ስህተቶች ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ እንዲሆን አይፈልጉም። ሕገ መንግሥቱ በእርግጠኛነት እርሳቸውን ነው መጀመሪያ ዒላማ የሚያደርጋቸው" ይላሉ አቶ ጳውሎስ

ሕገ መንግሥቱ እኛን አይወክልም የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ዶ/ር በረከት ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያታቸው ሕገ መንግሥቱ በሚረቀቅበት ወቅት ፈጽሞ ባለመሳተፋቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ሌሎች ደግሞ በበኩላቸው ሕገ መንግሥቱ የተጻፈበት መንገድ ለፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ስልጣን በሰጠ መልኩ ነው በሚል እንደሚቃወሙ ነው ዶ/ር በረከት የሚናገሩት። በተጨማሪም ሌላ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ መሬትና ቋንቋን የሚመለከቱ ጉዳዮች በአግባቡ ስላልተፈቱ መከለስ አለበት ይላሉ።

"በማርቀቅ ሂደቱ ውስጥ አልተካተትንም የሚሉ አካላት ተቃውሞ ተቀባይነት አለው" የሚሉት ዶ/ር በረከት፣ ሕገ መንግሥቱን የመከለስ፣ የመደመርና የማዘመን ሞራላዊ ግዴታ አለብን ሲሉም አክለዋል።

ሕገ መንግሥት አለመኖሩ ያስከተላቸው መዘዞች

"ሕገ መንግሥት አለመኖሩ የሚያስከትለው መዘዝ ግልጽ ነው" ይላሉ አቶ ጳውሎስ። እያየን ያለነው አምባገነንነት የዚያ ውድቀት ቀጥተኛ ውጤት መሆኑንም አክለዋል።

"አምባገነኖች ሥልጣን ላይ የሚቆዩት ሕግና ሥርዓትን በማፍረስ ነው። ኤርትራ ውስጥ እየሆነ ያለውም ነገር ይህ ነው" በማለት ህዝቡ እንደገና ስልጣን መቆጣጠር ከቻለ የአምባገኖች አወዳደቅም ክፉኛ መሆኑን ይናገራሉ።

ዶ/ር በረከት በአውሮፓውያኑ 2003 የነበረውን የአረብ ስፕሪንግ አብዮት ሃይል ጠቅሰው "ህዝቡ በጽናት አሁንስ ይበቃል ማለት ከቻለ የሚመጣውን ማዕበል ማንም ሊያቆመው አይችልም" ብለዋል።