ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዝንጀሮ ፈንጣጣ፡ በ12 አገራት 80 ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል- የዓለም ጤና ድርጅት
በ12 አገራት ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ) መያዛቸው መረጋገጡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የአገራቱን ስም ሳይገልጽ ሌሎች 50 ተጠርጣሪዎችም በምርመራ ላይ መሆናቸውንም የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
መጀመሪያ በአውሮፓ መታየቱን ተከትሎ ቀደም ሲል በጣሊያን፣ በስዊድን፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በዩናይትድ ኪንግደም በሽታው መኖሩ ተረጋግጧል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በብዛት በመካከለኛው እና በምዕራብ አፍሪካ አካባቢዎች በብዛት የሚከሰት ነው።
የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት እንደገለጸው፣ ይህ ያልተለመደ የቫይረስ ኢንፌክሽን አብዛኛውን ጊዜ ቀላል ሲሆን ብዙዎች ላይም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሚድን ነው።
ቫይረሱ በሰዎች መካከል በቀላሉ የማይሰራጭ ሲሆን በሰፊው ሕዝብ ጤና ላይ የሚያስከትለው ስጋት በጣም ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተለየ ክትባት የለም። ከመደበኛው ፈንጣጣ ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው የፈንጣጣ ክትባት 85 በመቶ የመከላከል አቅም ይሰጣል።
የዓለም ጤና ድርጅት አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ "በቅርብ ጊዜ በ11 አገሮች የተመዘገበው ወረርሽኞች ተላላፊ ባልሆኑ አገሮች ውስጥ መከሰቱ ያተለመደ ነው" ብሏል።
"ተጎጂዎችን ለማግኘት፣ ለመደገፍና የበሽታ ክትትልን ለማስፋፋት ከተጎዱት አገራት እና ከሌሎች ጋር እየሠራሁ ነው" ብሏል።
በተጨማሪም ድርጅቱ በበሽታው ምክንያት ማግለል እንዳይኖር አስጠንቅቋል።
"ማግለል ወረርሽኙን ለማስቆም እንቅፋት ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ሰዎች ሕክምና እንዳያገኙ ሊከለክል ይችላል። ወዳልታወቀ ስርጭትም ይመራል" ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዳይሬክተር ሃንስ ክሉጅ "ወደ በጋ ወራት ስንገባ ስብሰባዎች፣ በዓላት እና ድግሶች፣ ስርጭቱ ሊያፋጠኑ ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከሰቱት በስተቀር ሁሉም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደነበረባቸው አካባቢዎች የጉዞ ታሪክ የላቸውም ብለዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የመጀመሪያው በሽታ ግንቦት ከሁለት ሳምንት በፊት ሪፖርት ተደርጓል።
በሽተኛው በቅርቡ ወደ ናይጄሪያ የተጓዘ እና ወደ እንግሊዝ ከመጓዙ በፊት በቫይረሱ እንደተያዘ ታምኖበታል ሲል የእንግሊዝ የጤና ጥበቃ ኤጀንሲ አስታውቋል።
በዩናይትድ ኪንግደም 20 የተረጋገጡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሳጂድ ጃቪድ አርብ ዕለት ተናግረዋል ።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ክትባቱን ገዝተው ለዝንጀሮ ፈንጣጣ "ከፍተኛ ተጋላጭነት" ላላቸው ሰዎች መስጠት እንደጀመሩ ተናግረዋል ።
የስፔን የጤና ባለሥልጣናትም ወረርሽኙን ለመቋቋም በሺህዎች የሚቆጠሩ የፈንጣጣ ክትባቶችን ገዝተዋል ሲል የስፔኑ ኤል ፓይስ ጋዜጣ ዘግቧል።
የአውስትራሊያ የመጀመሪያ በበሽታው የተያዘ ሰው ወደ እንግሊዝ ከተጓዘ በኋላ ተገኝቷል ሲል የቪክቶሪያ የጤና ጥበቃ ዲፓርትመንት አስታወቀ።
በሰሜን አሜሪካ በዩናይትድ ስቴትስ የማሳቹሴትስ ግዛት የጤና ባለሥልጣናት አንድ ሰው በቅርቡ ወደ ካናዳ ከተጓዘ በኋላ በቫይረሱ መያዙን አረጋግጠዋል።
"በጥሩ ሁኔታ" ላይ እንዳለ እና "ለሕዝብ ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለው" ባለሥልጣናት ተናግረዋል።