ፋይዘር ውስጥ በኃላፊነት የምትሰራው ዶክተር አይዳ ኃብተጽዮን ማን ነች?

ትውልደ ኤርትራዊቷ እና በዜግነት ካናዳዊ የሆነችው ዶ/ር አይዳ ኃብተጽዮን ሃኪሞችንና ተቆጣጣሪ ድርጅቶችን ደህንነቱ የተጠበቀና አግባብ የሆነ የመድሃኒት አጠቃቀምን በተመለከተ መረጃ የሚሰጠውን ፋይዘር የህክምናና የደህንነት ዓለም አቀፍ ድርጅትን ትመራለች።

ኤርትራ ተወልዳ ያደገችው ዶ/ር አይዳ ሃብተጽዮን ከአልበርታ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከጉሌፍ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ምግብ ማስተርስ ዲግሪ አግኝታለች።

ካናዳ፣ ኦንታሪዮ ከሚገኘው ማክማስተር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የሕክምና ዲግሪዋን ይዛለች።

ዶክተር አይዳ በዌስተርን ኦንታርዮ ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ደዌ ህክምና እንዲሁም ከቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ካናዳ በጋስትሮ ኢንተሮሎጂና ሄፓቶሎጂ ክሊኒካዊ የተልዕኮ ፕሮግራም ሰርታለች።

ዶ/ር አይዳ ሃብተጽዮን ስራዎችዋን እና ጥናቶቿን በተመለከተ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረገችው ቃለመጠይቅ ስለ 'ፋይዘር' ድርጅት፥ ስለ ስነቅመማ-መድሃኒትና ባዮቴክኖሎጂ ስሪቱ እንዲሁም ድርጅቱ ውስጥ ስላላት ሚና አብራርታለች።

ፋይዘር አለምን በታደገው የፀረ ኮቪድ ክትባት ከፍተኛ ዝና እንዳገኘና ዶ/ር አይዳም በስራዎቹና ዘመቻዎቹ በመሳተፏ ትልቅ ስም ማግኘት ችላለች።

ስታንፎርድ በተባለ ታዋቂ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የህክምና መምህር ሆና ስትሰራ የቆየች ሲሆን በፋይዘር ኮርፖሬሽን ተለይታ ተቀጥራ በዓለም አቀፍ ስራዎቻቸው ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።

'ልጅነቴን ያሳለፍኩት ቤት ውስጥ ተዘግቼ ነው'

ዶ/ር አይዳ የተወለደችውና ያደገችው አስመራ ነው።

አስመራ ውሰጥ ስለነበራት አስተዳደግ፡ ቤተሰብ እና ትምህርቷ ትዝታዎቿ ስትናገር በናፍቆት ነው።

በአስመራ ካምቦኒ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው ዶ/ር አይዳ "ለኔ ቤተሰቤና አስተዳደጌ ብዙ ትርጉም አለው" ትላለች።

ስለ ተማረችበት ትምህርት ቤትም ስትናገር "ካምቦኒ በናፍቆት ነው የማስታውሰው።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ካምቦኒ የሴቶች ትምህርት ቤት ውስጥ ነው ያጠናቀቀችው።

"የተወለድኩት ከትልቅ ቤተሰብ ነው፣ የቤተሰቡ አባላት ተንከባክበው ነው ያሳደጉኝ፡" ስትልም ስለ ቤተሰቦቿ ትመሰክራለች።

ዶ/ር አይዳ ተማሪ በነበረችበት ወቅት በኤርትራ ስለ ነበረው ህይወት፥ ጦርነት እና ሽብር ታስታውሳለች።

"ከፍርሃት የተነሳ አስመራ በነበርኩበት ጊዜ ሰዓት እላፊ ስለነበር በማታ ስወጣ አላስታውስም። በነበረው ግርግር፡ ግፍ እና እስራት ምክንያት ልጅነቴን ያሳለፍኩት ቤት ውስጥ ተዘግቼ ነው። አስመራን በማታ ሳያት ትዝ አይለኝም፡" ትላለች።

"ይሁን እንጂ መልካም ጎኑን ማጣጣም ችያለሁ። የህብረተሰቡ ሁኔታ ልቤ ውስጥ ታትሟል፝" የምትለው ዶክተር አይዳ ከሚቀርቧት ከጓደኞቿ ጋር ስለሳቁባቸው ጊዜያቶች ስለተጫወቷቸው ስታስታውስ ትናንት የነበረ ያህል ሆኖ እንደሚሰማት ታስረዳለች።

አባቴ እንዲህ ሲል አስታውሳለሁ "ስራ ለሰው ልጅ ህይወቱ፡ ሞት ደግሞ እረፍቱ" በማለት ዛሬ በሕይወቷ ለስራ ኣላት ጥንካሬ እና ብርታት ምንጭ ቤተሰቦቿ መሆናቸውን ትናገራለች።

"በህይወቴ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ቤተሰቤ ነው፣ ቤተሰቤ በኔ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ስለትምህርት አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ፍቅርና ስራ ከፊት አሰልፈው ነው ያሳደጉኝ። የስራ ስነምግባር ደግሞ ህይወቴን በአግባቡ እንድመራ አግዞኛል። ትልቁ ውርስ በርትቶ መስራት፥ ሰው ማክበር እና ትምህርትን አለመርሳት አውርሰውኛል"

ዶ/ር አይዳ ስለራሷ ስትናገር፣ 'የተነሳሽነት ባህሪ ያለው ሰው መሆኔን ልናገር እፈልጋለሁ' ትላለች።

"ይህ ከፍተኛ ፍላጎት ነው፤ እንዲሁም ምኞቴንና ህልሜን ለማሳካት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ"

አክላም "ሰዎች የሚገጥማቸውን ፈተና ተቋቁመው ሊነሱና ሊወድቁ ይችላሉ፣ ነገር ግን ፈተናውን አዎንታዊ በሆነ መንገድ እጠቀምበታለሁ፤ ፍላጎቴንና ችሎታዬን ከፍ ለማድረግ እጠቀምበታለሁ" ትላለች።

"ሰው በጣም አስፈላጊ የሆነ አጀንዳ ለይቶ ማወቅ አለበት እላለሁ፤" የምትለው ዶ/ር አይዳ፣ ማንም ሰው የሕይወቱን መሪ ኮከብ ፈልጎ ማግኘት እና እርሱን ያለማወላወል መከተል እንደሚገባው ትገልጻለች።

"ሁላችንም የተለያየ ሰብዕና ስላለን የግድ እኔ ባለፍኩበት መንገድ ይለፍ አልልም። የሚያስፈልጉ ነገሮች ተገንዝቦና ለይቶ አቅምን መዝኖና ፍላጎትን አጠንክረህ መያዝ ነው እላለሁ።"

ኃላፊነት እና የዕለት ተዕለት ስራ?

ዶ/ር አይዳ ስለስራዋ ስትናገር ከዋናዎቹ ኃላፊነቶቿ ውስጥ ፋይዘር የሚፈጥራቸውና የሚያከፋፍላቸው መድሃኒቶችን፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ አገሮች በአግባቡ እንዲጠቀሙበት በቂ መረጃ መስጠትና ተገቢ ቦታ እንዲይዝ ማድረግ እንደሆነ ትናገራለች።

ፋይዘር ትልቅ ስምና ዝና ያለውና በመላው ዓለም ቅርንጫፎች አሉት። ከዚህም ጋር ተያይዞ የዶ/ር አይዳ ስራዋም ዓለም አቀፋዊ ነው።

ዶ/ር አይዳ በመላው ዓለም ካሉ የጤና ኃላፊዎች፣ የጤና ድርጅቶች፣ ተመራመሪዎች ጋር በመገናኘት አስፈላጊ መረጃ የምትሰበስብና የምታከፋፍል ተመራማሪ ናት።

"በሰፊው አጥብቄ የምከተላቸው የጊዜ ገደብ ያላቸው ('deadlines') ስራዎች አሉኝ። ማሟላት ያለብኝ አስፈላጊ ምእራፎች 'milestones' አሉኝ፣ ለምሳሌ ሁሉም አገሮች የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ክትትል አካሂዳለሁ፡" ትላለች።

አሁን ስላላት ኃላፊነት እና በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ስለምትሰራው ስራ ያለው አንድነትና ልዩነት ስትገልፅ

"እርግጥ ነው ይለያያል። በስታንፎርድ የአካዳሚ (ትምህርት ላይ ያተኮረ) ስራ ነበር የምሰራው፤ ጎን ለጎን የራሴን ምርምሮች ማካሄድ፥ ጽሑፎችን ማዘጋጀት፥ ማስተማር፥ በህክምና ትምህርት ዘርፍ ደግሞ ተባባሪ ዲን ሆኜ ነው የማገለግለው። በመሰረቱ ግን አሁን ከፋይዘር ጋር ከምሰራው ስራ አይለይም፡" በማለት ታስረዳለች።

"ስታንፎርድ ውስጥ የቀሰምኩት ክህሎቶች እዚህም እጠቀምበታለሁ። እዚያ የአካዳሚ ስራዎች፤ እዚህ ደግሞ በበለጠ ሳይንስ ላይ የተመረኮዙ ስራዎችን እሰራለሁ" በማለት ትገልፃለች።