ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በ69 ዓመታቸው ዩኒቨርስቲ ለመግባት የበቁት ኢትዮጵያዊው የ11 ልጆች አባት
መደበኛ ትምህርት ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሦስት የኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር ዘመናትን ተሻግሯል።
ከደርግ እስከ ኢሕአዴግ ከዚም አልፎ እስከ ብልፅግና።
አቶ ታደሰ ጊቺሌ ይባላሉ። የተወለዱት ምዕራብ ወለጋ ነው።
አርሶ አደር ናቸው። በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ በራሳቸው ሻይ ቤት ውስጥ ይሠራሉ።
ከሰሞኑ የአቶ ታደሰ ታሪክ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።
በ69 ዓመታቸው ጅማ ዩኒቨርስቲን በመጀመሪያ ዓመት ተማሪነት መቀላቀላቸው ነው ዝነኛ ያደረጋቸው።
እናት እና አባታቸው የሞቱት እሳቸው ገና ልጅ ሳሉ ነበር። በመደበኛ ትምህርት ዘልቆ ኮሌጅ የመበጠስ ሕልማቸው ወላጆቻቸውን በሞት ሲነጠቁ ተሰናከለ።
"በድሮ ጊዜ፣ አባትና እናቴ በልጅነቴ ስለሞቱብኝ መማር አቃተኝ" ይላሉ።
ያኔ በደርግ ዘመን እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ሲጣልባቸው ግን የሚወዱትን ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዱ።
ትዳር ከመሠረቱ በኋላ በዘመነ ኢሕአዴግ ወደ ትምህርት ቤት ተመለሱ። ግን ሊዘልቁበት አልተቻላቸውም።
"ሚስት ካገባሁ በኋላ ደግሞ ልጆች ስለበዙብኝ በፕሮግራም በፕሮግራም [እየተማርኩ፣ እያቋረጥኩ] ቀጠልኩ።"
ከዓመታት በኋላ ወደ ትምህር ቤት ቢመለሱም "ብዙ ችግሮች ስለገጠሟቸው" ወደ ግብርና እንደተመለሱ ይናገራሉ።
የ69 ዓመቱ ታደሰ ለፈተና እጅ አልሰጡም።
በ2005 ዓ.ም. ከስምንተኛ ክፍል ትምህርት ቀጠሉ።
"ዘመናዊ ትምህርት አላጣም ብዬ ወደ 8ኛ ክፍል ተመልሼ ተፈተንኩ. . . ከዚያም ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍልን ተማርኩ።"
አምና ወደ ሕልማቸው አንድ እርምጃ ተቃርበው፣ መልሶ ከሸፈባቸው።
"አምና 12ኛ ክፍል ተፈተንኩና ለአንድ ነጥብ ወደቅኩ።"
አልረታም ብለው ዘንድሮ በግላቸው፣ በድጋሚ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ተፈተኑ። 502 አምጥተው አለፉ።
"በግል ሞልቼ ስፈተን፣ እግዚአብሔር አጋጥሞኝ 502 አምጥቼ አለፍኩ።"
ለዘመናት ያልቀዘቀዘ የትምህርት ፍቅር
አሁን ጅማ ዩኒቨርስቲን በመጀመሪያ ዓመት ተማሪነት ተቀላቅለዋል።
ከድሮውም ትምህርት በጣም እንደሚወዱ ይናገራሉ።
"ድሮ የትምህርት ናፍቆትና ፍላጎት ነበረብኝ። ሰው የደረሰበት መድረስ አለብኝ። ለምን? ቢባል ለወደፊት ብዙ ዕቅዶች አሉኝ። የተማረ ሰው ነው ሁሉንም ነገር መሥራት የሚችል።"
ወደኋላ ተመልሰው ሲያስቡት፣ እናት እና አባት ቢኖራቸው ኖሮ "አቻዎቼ የደረሱበት ቦታ እደርስ ነበር" በማለት ይቆጫሉ።
አቶ ታደሰ የ11 ልጆች አባት ናቸው።
እሳቸው የሚወዱትን፣ የሚመኙትን ትምህርት በልጆቻቸው ለማሳካት ያደረጉት ጥረት በከፊልም ቢሆን የሰመረላቸው ይመስላል።
"ከ11ዱ ልጆቼ አንዱ አዲስ አበባ ፋብሪካ ውስጥ ይሠራል። ሁለተኛው ደግሞ አምና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተመርቆ ሥራ እየፈለገ ነው። ሌሎቹ 8ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አፀደ ህጻናት ይማራሉ። አራቱ ልጆቼ ግን አግብተዋል። አንማርም ብለው። ከባለቤቴ ጋር ብቻ ተመካክረን እናንተን የሚያገባ የለም ብዬ ነገርኳቸው።"
እሳቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአባትነት፣ ከግብርና እና ከሻይ ቤት ሥራ ጋር አጣጥመው ነው ያገባደዱት።
ማልደው 11 ሰዓት ይነሳሉ። የእርሻ መሬታቸውን አዘጋጅተው 2፡30 ላይ ወደ ትምህር ቤት ያመራሉ።
ከሰዓት ደግሞ ወደ እርሻቸው ይመለሳሉ።
"እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ትምህርት ቤት ከእኛ ቅርብ ነው። 10 ደቂቃ ይወስዳል። እርሻዬም ከቤቴ 25 ደቂቃ ነው የሚርቀው። ጠዋት 11 ሰዓት ተነስቼ እርሻዬን አዘጋጅቼ ወደ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ። ከዚያ ዘጠኝ ሰዓት ተመልሼ በሬዎችን ጠምጄ አርሳለሁ። ቡና እተክላለሁ።"
ቀኑን በትምህርት እና በግብርና አሳልፈው ማታ ማታ ያጠናሉ።
ልጆቻቸው ከተኙ በኋላ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ነው የሚያጠኑት።
ትምህርትን በሦሰት የአስተዳደር ዘመኖች ፈትሸውታል። በደርግ ዘመን የነበረው ከአሁኑ ቢለያይም አልከበዳቸውም።
"ለምሳሌ ሒሳብ [የያኔውና የአሁኑ] ይለያያል. . . እነ ፊዚክስና ኬምስትሪ አይከብዱኝም። በደንብ አጠናለሁ።"
ሻይ ቤት ሲሠሩ ጎን ለጎን ያጠናሉ። ከዕድሜና ከኃላፊነት መብዛት የተነሳ እንደው አቶ ታደሰ አይደክማቸውም?
"አይደክመኝም። የጉልበት ሥራ ራሱ ስፖርት ነው። ሻይ ቤት እሠራለሁ። እስከ 4 ሰዓት ደግሞ ዳቦ አቦካለሁ። ደብተሬን ወስጄ እዚያ ቁጭ ብዬ ማጥናት ብቻ ነው። ደስታ ይሰማኛል።"
ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው በትምህርት መግፋታቸውን ይደግፋሉ።
"ያንተ ጓደኞች የደረሱበት ለመድረስ ትሠራለህ እያሉ ፈቀዱልኝ። ችግር የለም። መግባባት አለ" ይላሉ።
ሐኪም ለመሆን አልመዋል
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ በአስተማሪዎቻቸው እንዲሁም አብረዋቸው በሚማሩ ወጣቶችም ሙገሳ ይቸራቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ይማሩ የነበረው ከእርሳቸው በዕድሜ በእጅጉ ከሚያንሱ ወጣቶች ጋር ቢሆንም ለመግባባትም ይሁን እንደ ወጣቶቹ ለመሯሯጥ እምብዛም አልቸገራቸውም።
"አስተማሪዎቹ ምስጋና ያቀርቡልኛል. . . ተማሪዎቹ ይደሰታሉ። አባታችን በመሐላችን ተቀምጠው ስለሚማሩ ተስፋ አግኝተናል። ከዚህ በኋላ ትምህርታችንን አናቋርጥም እያሉ በጣም፣ በጣም ይንከባከቡኛል። ከልጆች ጋር ኳስ እጫወታለሁ። ድሮም ስፖርተኛ ነበርኩኮ! አይከብደኝም። በጣም ደስ ይለኛል።"
እሳቸውም እንደ ታላቅነታቸው ወጣቶቹን ይመክራሉ።
". . .ትምህርት ሳትወዱ ሜዳ ላይ ተንከራታችሁ ጫትና አልኮል ከምትጠጡ፣ ቁማር ከምትጫወቱ፣ ባልሆነ ቦታ በአሉባልታ ከምትውሉ እባካችሁን ትምህርታችሁን ተከታተሉ። የተማረ ሰው ሁሉንም ነገር ሊፈጽም ይችላል። የተማረ ሰው የፈለገውን ሊያገኝ ይችላል። አገር ሊያስተዳድር ይችላል። ፕሮፌሰር መሆን ይቻላል። ሐኪም መሆን ይችላል. . . "
የአቶ ታደሰ ሕልም ሐኪም መሆን ነው።
ከስድስት አሥርታት ትግል በኋላ አስኳላ በመግባታቸው "እግዚአብሔርን አመሰግናሉ" ይላሉ።
"የምመኘው፣ ከተሳካልኝ ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ። ለምን? ካልሽኝ፣ ብዙ ሰው እንድረዳ ነው እሱን የመረጥኩት።"
ትምህርት ዕድሜ ይገድበዋል ባይባልም ፈተናዎችን ሁሉ አልፈው ከአንድም ሁለት ሦስቴ ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ምን አበረታቸው? የ69 ዓመቱ የጅማ ዩኒቨርሰቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ መልስ አላቸው።
". . . ልማት ለማስፋፋት ከሆነ በትምሀርት ነው፤ ሱቅ ለማግኘት ከሆነ በትምህርት ነው፤ ፋብሪካ ለማቋቋም ከሆነ በትምህርት ነው፤ አልፎም አገር ለመርዳት፣ ሕዝብ ለማገልገል ትምህርት ያስፈልጋል። ያለ ትምህርት ምንም የሚሳካ ነገር የለም። ልቤና አንጎሌ አንዲያድግ እማራለሁ!"