በሶማሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ማን ናቸው?

የመሪነት ሥልጣንን ሲጨብጡ የመጀመሪያቸው አይደለም።

እአአ ከ2012 እስከ 2017 የሶማሊያ ስምንተኛው ፕሬዝዳንት ነበሩ።

በ2017 በድጋሚ ሲወዳደሩ ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ረቷቸው።

በቀውስ በምትናጠው የአፍሪካ ቀንድ አገር ሶማሊያ በድጋሚ በመመረጥ ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ታሪክ ሠርተዋል።

የትላንቱ ምርጫ በአገሪቷ ታሪክ ፉክክር የበዛበት ነበር። የምርጫ ሂደቱ በሦስት ዙር ተካሂዷል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት በትምህርት ዘርፍ ይታወቃሉ። የምረጡኝ ቅስቀሳቸው ማጠንጠኛ ሶማሊያን ከተቀረው ዓለም ማስታረቅና የሕዝቡን አንድነት ማረጋገጥ ነው።

በበዓለ ሲመታቸው የተናገሩትም ይህን ሕልማቸውን ነው።

"ከቀጠናውና ከዓለም አቀፍ አካላት ጋር በቅርበት እንደምንሠራ ቃል እገባለሁ" ብለዋል።

ከድምጻቸው እርቅ ይስተጋባል። ለእያንዳንዱ የሶማሊያ ዜጋ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

በሦስተኛው የድምጽ መስጫ ደረጃ በ214 አብላጫ ድምጽ፣ 110 ድምጽ ያገኙትን ፋርማጆ አሸንፈዋል።

2017 ላይ ያሸነፏቸው ፋርማጆን በ2022 መልሰው አሸንፈዋቸዋል።

ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያሳለፉት በሞቃዲሾ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ነው።

ፋርማጆ ሥልጣናቸውን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለማራዘም ሲሞክሩ ከተቃወሙ መካከል ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ አንዱ ናቸው።

አምና የፀጥታ ኃይል አባላት ቤታቸውን ከፈተሹ በኋላ መነጋገሪያ ሆነዋል። ፍተሻው የተካሄደው ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ በወጠኑበት ወቅት ነበር።

ሶማሊያ ለ30 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥ አገሪቱን ጥለው ካልሄዱ ጥቂት መሪዎች መካከልም አንዱ ናቸው።

ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከፍተኛ ድርቅን ጨምሮ በበርካታ ችግሮች የተሸበበች አገር ነው ከፋርማጆ የሚረከቡት።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፣ ድርቁ ካልተገታ ወደ ረሃብ ከፍ ሊል ይችላል።

ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሩሃብ አፋፍ ላይ ሆነው አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ይጠብቃሉ።

ሶማሊያን የኑሮ ውድነትና የዩክሬን ጦርነት ያባባሰው የዋጋ ግሽበትም ይፈትናታል።

በፌደራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል እየሰፋ ያለው ልዩነትም ሌላው የሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ የቤት ሥራ ይሆናል።

ሙስና ሌላው የሶማሊያ ማነቆ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት አዲሱ ፕሬዝዳንት አገራቸው ከኬንያ፣ ጂቡቲ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን ግንኙነት የማደስ ኃላፊነትም ተጥሎባቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት የሶማሊያ እና ኬንያን ግንኙነት ቆርጠዋል። አገራቱ በባሕር ወሰንም ይወዛገባሉ።

ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ 2012 ላይ ሲመረጡ አገራቸው ከምዕራባውያን እና ከአፍሪካ አገራት ጋር መደበኛ የዲፕሎማሲ ትስስተሯን እንድታድስ አስችለዋል።

በሌላ በኩል በአስተዳደራቸው ስር ያለውን ሙስና ማስወገድ አልቻሉም ተብለው ይታማሉ።

የተወለዱት እአአ በ1955 ሂራን ግዛት ነው። በሞቃዲሾ በመካከለኛው መደብ ሰፈር አድገው ከሶማሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ በምህንድስና በ1981 ተመርቀዋል።

በቅርብ የሚያውቋቸው ዝምተኛና የማይታበዩ ሰው ናቸው ይሏቸዋል።

ሁለተኛ ዲግሪ ከመሥራታቸው በፊት በሕንድ ቦሆፓል ዩኒቨርስቲ አስተማሪ ነበሩ።

ወደ ሶማሊያ ሲመለሱ በተባበሩት መንግሥታት የተዘረጋውን የመምህራን ሥልጠና ለመምራት በትምህርት ሚኒስቴር ተቀጠሩ።

በ1991 ማዕከላዊው መንግሥት ሲንኮታኮት፣ በዩኒሴፍ የትምህር ኃላፊ ሆነው ተቀጠሩ።

በደቡብና ማዕከላዊ ሶማሊያ ይዘዋወሩ ነበር። ወቅቱ በትምህርት ዘርፍ ያለውን ውድቀት በቅርበት ያስተዋሉበት ነበር።

ከሦስት ዓመታት በኋላ፣ በሞቃዲሾ ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ ግንባር ቀደም ከሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንዱን ከፈቱ።

የሙስሊም ወንድማማችነት (Muslim Brotherhood) የሶማሊያ ቅርንጫፍ የሆነው አል-ኢላህ ጋር ግንኙነት አላቸው።

የጎሳ ግጭት በተነሳበት ወቅት ለማኅበረሰቡ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ቡድኑ በግብፅና ሱዳን ጋር በተመሳሳይ በሆነ የእስልምና አስተምህሮት የሚተዳደር ትምህርት ቤቶች ከፍቷል።

እንደ አል-ሸባብ እና አል-ቃይዳ ያሉ አክራሪዎችንም ያወግዛል።

ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ "ለዘብተኛ ሙስሊም" ተብለው ይታወቃሉ።

በጦርነት የደቀቀችውን ሶማሊያ ለመደገፍ በንግድ ሰዎች የተቋቋመው 'ዩኒየን ኦፍ ኢስላሚክ ኮርትስ' ከተባለው ፍርድ ቤት ጋርም ትስስር አላቸው።

ፍርድ ቤቱ በ2006 ለአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል።

አል-ሸባብ በፍርድ ቤቱ ያለው ጫና እየጨመረ መሄድ ያሰጋት ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቱን የሚቀለብስ እርምጃ መውሰዷ ይታወሳል።

የአዲሱ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች እንደሚሉት፣ ሰላምና መረጋጋትን ለመመለስ የሚሠሩ መሪ ናቸው።

በ1990ዎቹ የሲቪል ማኅበራት ውስጥ ከፍተኛ ንቅናቄ ያደርጉ ነበር። የጎሳ ግጭትን በማርገብም ይታወቃሉ።

ሞቃዲሾን ለሁለት ሰንጥቆ በሁለት ተፎካካሪ ጎሳዎች እንድትመራ ያደረጋት "ግሪን ላየን" የተባለውን አካሄድ ለማፍረስ በተደረገው ድርድር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ይህ አካሄድ "የሞቃዲሾ ካንሰር" ተብሎ ይጠራ ነበር። ለነዋሪዎችና ለፖለቲከኞችም ሕይወትን ፈታኝ አድርጓ ቆይቷል።

በሽግግር አስተዳደር ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካሪ ነበሩ።

በ2001 ከግጭት በኋላ እርቅ ለማውረድ የሚጥረው የ'ሴንተር ፎር ሪሰርች ኤንድ ዳያሎግ' አጥኚ ሆነው ተቀጥረዋል።

ይህ ማዕከል ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባለው ቅርርብ ይተቻል።

ሆኖም ጥናቶቻቸው ሶማሊያን ከ30 ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ለማውጣት ያግዛሉ ተብሎ ይታመናል።