ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝደንት የነበሩት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ዳግም ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ።
አዲሱ ተመራጭ ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ እአአ ከ2012-2017 የሶማሊያ 8ኛው ፕሬዝደንት በመሆን አገልግለዋል። ተመራጩ ፕሬዝዳንት ተቀናቃኛቸውን ተሰናባች ፕሬዝዳንት መሐመድ ፋርማጆን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡
ፋርማጆ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ አገሪቱን እየመሩ ቆይተዋል፡፡
ትናንት የመጨረሻው ዙር ምርጫ የተደረገው 328 የፓርላማ አባላት በሰጡት ድምጽ ሲሆን ከነዚህ የሕዝብ ተወካዮች አንዱ ድምጽ አልሰጡም፡፡
በሦስተኛው ዙር ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከሕዝብ ተወካዮች 214 ድምጽ ሲያገኙ ፋርማጆ ግን 110 ድምጽ ብቻ ነው ያገኙት፡፡
ሦስት ተወካዮች ድምጻቸው ተስተጓጉሏል፡፡
ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ ከ2012 እስከ 2017 ዓ/ም ድረስ አገሪቱን መርተዋል፡፡
ከዚያ በኋላ አሁን ተሰናባች በሆኑት ፋርማጆ ተሸንፈው ነበር ሥልጣን የለቀቁት፡፡
የእሁዱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትና ሦስት ዙር ድረስ የሄደ ሲሆን ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና የፀጥታ ጉዳይ ምርጫው መደረግ ከነበረበት በ15 ወራት ዘግይቶ እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ የመጨረሻ ውጤቱ ከመታወጁ ጥቂት ቀደም ብለው ማሸነፋቸውን በማወጃቸው ደጋፊዎቻቸው በዋና ከተማዋ ደስታቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል፡፡
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት አገሪቱን ይመራሉ፡፡
ትናንት እሑድ የተደረገው ምርጫ በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ የተካሄደ ሲሆን ምርጫው ከሚደረግበት ቦታ በቅርብ ርቀት መጠነኛ ፍንዳታ ተሰምቷል፡፡ ሆኖም ፖሊስ የከፋ ጉዳት አልደረሰም ብሏል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ፀጥታን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በሶማሊያ የተከሰተውና ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለረሀብ ለዳረገው ድርቅ መፍትሄ ማፈላለግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሶማሊያ የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ እንደ ብዙ አገሮች ሁሉ በነዳጅና ሸቀጦች ዋጋ መናር ፈተና እያየች ነው፡፡ ይህንን ምጣኔ ሀብት ማረጋጋትም የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዋና ሥራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሶማሊያ መንግሥት አል-ሸባብን በመዋጋት ረገድ 18ሺህ በሚሆኑ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ያዋጣቸው ወታደሮች ይደገፋል፡፡
ይህ የፀጥታ ችግር ነው ሶማሊያ ቀጥተኛ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳታደርግ ምክንያት የሆናት፡፡
ሶማሊያ እንደ አውሮፓዊያኑ ከ1969 ወዲህ በቀጥታ ፕሬዝዳንታዊ የሕዝብ ምርጫ አላደረገችም፡፡
ይህ የአሁኑ ቀጥተኛ ያልሆነ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገ ሲሆን ቀደም ያሉ ምርጫ አሰጣጦች በፀጥታ ችግር የተነሳ በኬንያና ጂቡቲ ነበር የተደረጉት፡፡
አዲሱን ፕሬዝዳንት ድምጽ በመስጠት የመረጡት የሕዝብ ተወካዮች የተመረጡት በአገሪቱ ዋንኛ ጎሳዎች በተወጣጡ ተወካዮች ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮቹ ምርጫቸውን ያደረጉት ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግለት አየር ማረፊያ ውስጥ በሚገኝ አውሮፕላን ማቆሚያ ውስጥ ነው፡፡ ይህ አውሮፕላን ማቆሚያ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ዋና ቀጠና ሲሆን የዲፕሎማሲና የእርዳታ ድርጅቶች የሚገኙበት አካባቢም ነው፡፡
ድምጽ አሰጣጡ ይደረግበታል ከተባለው ሰዓት የዘገየ ሲሆን ይህም የሆነው ጥብቅ ፍተሻ ይደረግ ስለነበረ ነው፡፡
ብቸኛዋ ሴት ዕጩ የነበሩት የቀድሞዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋውዚያ ዩሱፍ አደም በመጀመርያው ዙር ተሸንፈው ከውድድር ውጪ ሆነዋል፡፡
ቀደም ብሎ በሚደረጉ ምርጫዎች አል-ሸባብ የጎሳ መሪዎችን ጭምር በማፈን፣ ጥቃት በማድረስ ምርጫ ያስተጓጉል ነበር፡፡
በዚህ ምርጫ አል-ሸባብ ዝምታን የመረጠ ይመስላል፡፡ ይህ ሁኔታ ለአንዳንዶች ስጋትን ጭሯል፡፡
ስጋታቸውም የአል-ሸባብ ወዳጆች የሆኑ ወደ ፓርላማ ሳይገቡ እንዳልቀረና ትግሉ ከውስጥ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡
ይህ ስጋት በጂቡቲው ፕሬዝዳንት በ2020 ዓ.ም. በግልጽ ተነግሯል፡፡ ኡማር ጉሌህ ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት አል-ሸባብ የሕዝብ ተወካዮችን በገንዘብ እየገዛ አገሪቱን በእጅ አዙር ሊቆጣጠር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠው ነበር፡፡
አንዳንድ ተንታኞች የጉሌህን ስጋት የተጋነነ ቢሉትም አል-ሸባብ አሁንም በሶማሊያ ትልቅ የፖለቲካ ኃይል መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም ይላሉ፡፡