ሩሲያ ጎረቤቴ ፊንላንድ ኔቶን ከተቀላቀለች የአጸፋ ርምጃ እወስዳለሁ ስትል ዛተች

ሩሲያ ጎረቤት አገር ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ከተቀላቀለች "የአጸፋ ርምጃዎችን" እወስዳለሁ ስትል ዛተች።

ከሞስኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ የፊንላንድ የኔቶ አባልነት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በእጅጉ ከመጉዳቱ ባለፈ ለሰሜን አውሮጳ ደኅንነት እና መረጋጋት አደጋ ነው ብሏል።

ቀደም ሲል የፊንላንድ ፕሬዝደንት እና ጠቅላይ ሚኒሰትር አገራቸው 'ሳትዘገይ' የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን በይፋ ማቅረብ ይኖርባታል ብለዋል።

ፊንላንድ ከሩሲያ ጋር 1300 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ድንበር ትጋራለች። ፊንላንድ በምስራቅ በኩል ካለችው ጎረቤቷ ሩሲያ ጋር ውጥረት ውስጥ ላለመግባት ከኔቶ አባልነት ራሷን ገድባ ቆይታለች።

ይኹን እንጂ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ከፊንላንድ በተጨማሪ ስውዲንም የኔቶ አባልነት ጉዳይን መልሳ እንድታጤነው አድርጓል።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ ፊንላንድ እና ስውዲን የኔቶ አባል እንዲሆኑ ፍላጎት አላቸው።

ፊንላንድ የአባልነት ጥያቄዋን የፊታችን እሁድ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ ስውዲንም የአባልነት ጥያቄዋን በተመሳሳይ ቀን ታቀርባለች ተብሎ ይጠበቃል።

የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶለተንበርግ ስውዲን እና ፊንላንድንም የኔቶ አባል የማድረጉ ሂደት 'በፍጥነት' ይካሄዳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ዋይት ሃውስ የሁለቱን አገራት የአባልነት ጥያቄ አሜሪካ እንደምትደግፍ አስታውቋል። ከዋይት ሃውስ በተጨማሪም የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ኔቶን የመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው ሪፖርቶች ሲጠቁሙ ነበር።

እንደ ማሳያም ባለፈው ሳምንት በፊንላንድ የተካሄደ መጠይቅ፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 76 በመቶ የሚሆነው ኔቶን መቀላቀል እንደሚፈልግል የገለጸ ሲሆን 12 በመቶ ደግሞ ውሳኔን አንቀበለውም ብለዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፊንላንድን የኔቶ የአባልነት ጥያቄ አጥብቆ በኮነነበት መግለጫው፤ "የፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄ የሩሲያ-ፊንላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነትን እጅጉን ይጎዳል። እንዲሁም ለሰሜን አውሮፓ ቀጠና መረጋጋት እና ሰላም አደጋ ይሆናል" ብሏል።

"ሩሲያ ከዚህ የሚከሰት የደኅንነት ስጋት ለማስወገድ ቴክኒካዊ የሆነ የጦር እና ሌላ መልክ ያለው የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች" የሚል ጠንከር ያለ መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አውጥቷል።

የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ ምክትል ተወካይ የሆኑትን ዲሚትሪ ፖለያንስኪ በመጥቀስ፤ ስውዲን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል ከሆኑ የሩሲያ ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ስለማለታቸው ዘግቧል።

ስውዲን እና ፊንላንድ ኔቶን ለምን ይቀላቀላሉ?

ከቀናት በፊት የፊንላንድ እና ስውዲን መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ የአገራቱ የኔቶ አባልነት ለደኅንነታቸው ማረጋጋጫ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኔቶ በአንዱ የአባል አገር ላይ ጥቃት ቢሰነዘር በሁሉም የአባል አገራት ላይ ጥቃት እንደተቃጣ አድርጎ ይቆጥራል።

በአሁኑ ወቅት ኔቶ 30 አባል አገራት አሉት። እነዚህም፦

አልባኒያ፣ ቤልጂየም፣ ቡልጋሪያ፣ ካናዳ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ አይስላንድ፣ ጣልያን፣ ላትቪያ፣ ሊቱዌኒያ፣ ላክሰዘምበርግ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሰሜን መቄዶኒያ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩሜኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬኒያ፣ ስፔን፣ ቱርክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ በአውሮጳውያኑ 1949 ላይ በ12 አገራት ነበር የተመሰረተው። በወቅቱ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያካትት ነበር።

አባል አገራት ወታደራዊ ጥቃት ከደረሰባቸው እርስ በርሳቸው ለመደጋገፍ ነው ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት።

አባል አገራት ከዚህ ስምምነት የደረሱት የሶቪየት ሕብረት አውሮጳ ውስጥ የመስፋፋት እቅድን ለመከላከል ያለመ ነበር።

እአአ 1955 ላይ ሶቪየት ደግሞ ለዚህ ስምምነት ምላሽ በሚመስል መልኩ የምሥራቅ አውሮፓ ኮምዩኒስት አገራት ጥምረት የሆነውን 'የዋርሶ ስምምነት' የተሰኘ ስብስብ አቋቋመች።

ነገር ግን እአአ 1991 ላይ የሲቪየት ሕብረት መፍረስን ተከትሎ በርካታ የዋርሶ ስምምነትን የፈረሙ አገራት ድርጅቱን እየለቀቁ ኔቶን መቀላቀል ጀመሩ።