በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይሆን?

ላለፉት 17 ወራት በጦርነት ሲናጥ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ከአፋር ወጥተናል ማለታቸውን ተከትሎ መረጋጋት ያሳየ ቢመስልም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ዳግም ግጭቶች ሊያገርሹ እንደሚችሉ እየታዩ ነው።

የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተው ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱን ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።

ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለው በራማ እና ባድመ አካባቢ ባለው የኤርትራ ጦር ላይ እሁድ ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ ጥቃቱን ተከትሎ በትግራይ ኃይሎችና በኤርትራ ጦር መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል።

ምንም እንኳ ከኤርትራ ወገን ስለነበረው የተኩስ ልውውጥ ማረጋጋጥ ባይቻልም አንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ለቢቢሲ ግጭቱ መከሰቱን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ በቦታው ተገኝተው የጎበኙ ሲሆን ወታደራዊ ብቃቱን የሚያሳይ ትርዒትም ተመልክተዋል።

ረቡዕ ዕለትም አማራ ክልል ፣ ባሕር ዳር ከተማ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የተለያዩ የፀጥታ አስከባሪ አካላት፣ የፋኖ አባላትና አመራሮች፣ በጦርነቱ የተሰዉ ግለሰቦች ቤተሰቦች፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና አመራሮች እንዲሁም የክልል መንግሥታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ምስጋና እና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በወቅቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ "ኢትዮጵያዊያን በፍጹም አገራቸውን አስደፍረው አያውቁም፣ አሁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፍጨረጨሩ ሁሉ ተስፋ ቆርጠው አርፈው እንዲቀመጡ አስረግጠን እንነግራቸዋለን" ማለታቸው ተዘግቧል።

የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ለዓለም አቀፍ ተቋማት በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ጦርነት አስቸኳይ መፍትሔ በማፈላለግ እንዲያግዙ እና በትግራይ ላይ ተጥሏል ያሉት ከበባ እንዲያበቃ ካልተደረገ "ሌላ አማራጭ" ለመፈለግ እንደሚገደዱ ገልፀው ነበር፤ ነገር ግን ይህ "አማራጭ" ያሉት ምን እንደሆነ በደብዳቤው ላይ አልተብራራም።

በዚህ ሰሞንም ከፍተኛ የህወሓት መሪዎች ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች እያካሄዱ ሲሆን ሊቀመንበሩ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በተገኙበት አንድ መድረክ ላይም "... በዚህ ሁኔታ ብለን መቀጠል አንችልም። ከሰሜን ሸዋ በኋላ ለሰላም እና ዲፕሎማሲ ዕድል ሰጥተናል። ከጦርነት በፊት እና በጦርነት ጊዜ ዕድል ሰጥተናል። ሁሉም ፖለቲካዊ ችግር በሰላም እና በዲፕሎማሲ ብቻ አያልቅም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ደብረፂዮን በዚህ መድረክ ላይ "መብታችንን ለማስከበር ሪፈረንደም ማካሄድ አለብን፤ የትግራይ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን አለበት" ማለታቸው ተጠቅሷል።

ዶ/ር ደብረፂዮን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ቢያንስ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ ዕድል መስጠታቸውን በማንሳት፤ ነገር ግን በቂ እርዳታ እየገባ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"ሕዝባችን እየተራበ ብቻ ሳይሆን እየታመመ እና እየሞተ ነው፤ ጊዜ እያለፈ ነው፤ በዚህ ሁኔታ መቆየት አንችልም። ለሁሉም ነገር ግን ዕድል ሰጥተን መላክ ያለበትን መልዕክት ለሚመለከታቸው አድርሰናል። ስለዚህ እኛ ጨርሰናል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ወደ ትግራይ የሚገባውን ሰብአዊ እርዳታ በተመለከተ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በይፋዊ ትዊተር ገጻቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት በትግራይ ክልል ላይ የጣሉትን እገዳ እንዲያነሱ እና ዕርዳታ እንዲገባ እንዲፈቅዱ ጠይቀው ነበር።

መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ተኩስ ካቆሙ 10 ሳምንታት እንደሆናቸው የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፣ እስካሁን ወደ ትግራይ የገባው ዕርዳታ ግን 5 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል።

ዶ/ር ደብረፂዮን በበኩላቸው ማዕከላዊው መንግሥት ተኩስ አቁሜያለው በሚል ከበባውን እየቀጠለበት ነው ሲሉ ይወነጅላሉ።

"መሳሪያ ለማሰባሰብ፣ ሠራዊት ለማሰባሰብ እና ለማዘጋጀት፣ ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች ለማቃለል ጊዜውን እየተጠቀመ ለወረራ እየተዘጋጀ ነው" ሲሉም በስብሰባው ላይ ለተሳተፉ ተናግረዋል።

ዳግም ጦርነት ያገረሻል?

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር) ሰሞኑን የትግራይ ኃይሎች ወደ ኤርትራ የከባድ መሳርያ ተኩስ አካሄዱ የተባለበትን ሁኔታ ሲያብራሩ፣ በትግራይ በኩል አስፈላጊውን ዓለም አቀፍ ትኩረት አላገኘንም በሚል ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

ከዚያም ባለፈ "ተስፋ በመቁረጥ፣ ከዚህ በላይ ሌላ አማራጭ የለንም በሚል የጦር ኃይል መጠቀም አለብን ወደሚል እሳቤ ገብተው ሊሆን ይችላል" የሚሉት አደም፣ በአካባቢው ጦርነት ተመልሶ የማገርሸት ዕድሉ አሁንም መኖሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዶ/ር አደም ጦርነት ዳግም የማገርሸቱ አደጋ ሁሌም የነበረ ነው ይላሉ፤ ጨምረውም ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እስካልተደረገ ድረስ ምናልባትም እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

"ጦርነት ባይፈለግም፣ እየተራበ የሚሞት ኅብረተሰብ የለም" የሚሉት አደም ካሴ፣ "ባይፈልግም ወደ ጦርነት መግባቱ የማይቀር ነገር ነው" ይላሉ።

አደም ካሴ (ዶ/ር) ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በቂ ጥረት እየተደረገ ነው ብለው አያምኑም። ለዚህም በአስረጅነት ያቀረቡት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ለማድረስ አሁንም አለመቻሉን ነው።

በተጨማሪም በሁለቱም ወገኖች መካከል የሚሰሙት መወቃቀሶች ወደ ሰላማዊ መንገድ ከማምጣት ይልቅ ጥርስ የሚያናክሱ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ሰላም ወደ ጎን ሊገፋ የሚችል አማራጭ አይደለም

እንደ ዶ/ር አደም የትግራይ ኃይሎች በኤርትራ በኩል ጦርነት የሚከፍቱ ከሆነ "ያሸነፈው የተሸነፈውን አካል ለማጥፋት ነው" ካሉ በኋላም ከዚህ ቀደም ሁለቱ አካላት ያላቸው ታሪክና ቁርሾ ለዚህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይላሉ አደም ይህ የመጠፋፋት ፖለቲካ ከዚህ ቀደምም የተሞከረ በመሆኑ "አብሮ መኖርን እንደማይለወጥ ነገር በመውሰድ በምን መልኩ አብረን እንኖራለን፣ እስከ ዛሬ የነበሩ ችግሮችን በምን መልኩ መፍታት እንችላለን" የሚለው በኤርትራ ብቻ ሳይሆን በፌደራል፣ በአማራ እና በአፋር በኩል መታሰብ እንዳለበት ያነሳሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ አደም (ዶ/ር) ሰላም ለሁሉም ጦርነት ተሳታፊዎች ወደ ጎን ሊገፋ የሚችል አማራጭ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

አክለውም ለ17 ወር የቀጠለው ጦርነት ያስከተለው ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ተባብሶ እንዳይቀጥል ስልታዊ የሆነ፣ በሚገባ የታሰበበት እና ሁሉንም አካላት ባሳተፈ መልኩ በቁርጠኝነት መሰራት እንዳለበት ይመክራሉ።

"በትግራይ ኃይሎች በኩል አሁን አማራጭ የለንም፤ እናሸንፋለን የሚል እሳቤ ቢኖርም ያንን የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው ብዬ አላስብም። ነገር ግን ብስጭታቸው ተገቢም ነው" ሲሉ ያክላሉ።

ይህንንም ሲያስረዱ በተለይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አለመሻሻሉ፣ በሰላማዊ መንገድ ለመሄድ ያለው ቁርጠኝነት ግልጽ አለመሆኑ፣ የእነርሱን ብስጭት መጨመሩ እና ትዕግስታቸውን መፈተኑ አይቀርም ይላሉ።

ሰው እየተራበ እና እየሞተ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አሳሳቢ መሆኑን የሚያስረዱት ዶ/ር አደም፣ "ቀስ እያሉ በትዕግስት ነገሮችን በተስፋ የሚያዩበት ሁኔታ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ነገር ግን በአፋር፣ በአማራ፣ በፌደራል እና በኤርትራ ኃይሎች በኩል ሰብአዊ እርዳታ ለተቸገረው ሕዝብ በእኩል እንዲደርስ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚጠበቅባቸውም ያብራራሉ።

በዚህ ጦርነት የትግራይ ኃይሎችም ሆኑ የተቀሩት የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ግባቸው ምን ሊሆን ይችላል ተብለው የተጠየቁት አደም ካሴ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ኃይሎች ከበባውን ተሰበረም አልተሰበረም "ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም" ሲሉ ያብራራሉ።

ትግራይ ያለችበት ሁኔታ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አለመድረስ እና የሰው ልጅ በረሃብ የተነሳ መሞት፣ ባይሳካላቸው እንኳ እንዲሞክሩ ገፊ ምክንያት እንደሚሆናቸው ዶ/ር አደም ያስረዳሉ።

በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሰብዓዊ እርዳታዎች በፍጥነት እንዲደርሱ ለማድረግ የሚያስችላቸውን እርምጃዎች በአፋጣኝ መውሰድ እንደሚያስፈልገውም ዶ/ር አደም ያነሳሉ።

የትግራይ ኃይሎችም ቢሆኑ ከአፋር ክልል ጠቅልለው መውጣት እንደሚኖርባቸው ያነሱት አደም ካሴ (ዶ/ር)፣ አፋር እና አማራ ክልሎችም ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተባባሪ መሆን ሌላ ዙር ጦርነት ለማስቀረት ይረዳል ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ንግግሩ በግልጽ እንዳይካሄድ የሚያደርገው ህወሓት ሽብርተኛ ተብሎ መፈረጁ መሆኑን ያነሱት የፖለቲካ ተንታኙ፣ ይህም ሊነሳ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ መፋቁ የሰላም ድርድሩ ያለ ተግዳሮት እንዲካሄድ በር ከፋች መሆኑን የሚገልፁት አደም ካሴ፣ የተወሰኑ መሠረታዊ አገልግሎቶችም በተወሰነ መልኩ እንዲመለሱ ዕድል እንደሚሰጥ አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የሚሰማው የጥላቻ ንግግር እና ፍረጃ መቆም እንዳለበት እንዲሁም ትኩረታቸውን ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።

ዘላቂ ሰላም ለምን ማምጣት አልተቻለም?

እንደ ዶ/ር አደም ለትግራይ ክልል ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ፈተና የሆኑት ጉዳዮች ሁለት ናቸው።

በአገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ ውስብስብነትን እንዲሁም በዓለም አቀፍ በኩል ደግሞ የዩክሬን ጦርነት እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደሚነሱ መሰማትን ጠቅሰዋል።

ጦርነቱን ያስጀመረው ጥላቻ በጦርነቱ ወቅት መባባሱን ያነሱት ዶ/ር አደም፣ አንደኛው በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ያሉ በርካታ ኃይሎች ያለባቸው ጫና፣ በውስጣቸው ያለ አለመተማመን እና ትኩረት ማጣትን በቀዳሚነት ያነሳሉ።

ሌላው ደግሞ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የዓለምን የትኩረት አቅጣጫ መቀየሩ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደሚነሱ መሰማቱ የሰላም ሂደቱ መንገራገጭ እንዲገጥመው አድርጓል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ተመልሳ ጦርነት አዙሪት ከገባች ከፍተኛ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ የሚያስከትል መሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ጦርነቱ እንደገና ከተጀመረ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ ተጨማሪ ጉዳት የሚያደርስ እንጂ ዋነኛው አለመሆኑን ዶ/ር አደም ይናገራሉ።

በቀጠናው ላይም ቢሆን የሱዳን አለመረጋጋት፣ ሶማሌ እና ኬንያ ምርጫ ላይ መሆናቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ትኩረት ስለሚከፋፍለው ግጭቱን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።