ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በህንድ በቡድን ተደፍራ ሪፖርት ልታደርግ የሄደችውን ታዳጊ ፖሊስ ደፍሯል መባሉ ቁጣ አስነሳ
በህንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በቡድን የተደፈረች አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ሪፖርት ልታደርግ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሄደችበት ወቅት በፖሊስ ተደፍራለች መባሉ ቁጣን ቀስቅሷል።
በፖሊሱ ላይ የወንጀል ክስ የተከፈተበት ሲሆን ከስራ መታገዱን አንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ታዳጊዋ ባለፈው ወር በአራት ሰዎች በቡድን መደፈሯን የተናገረች ሲሆን አክሎም የታዳጊዋ በፖሊስ ተደፍራለች መባሉ ከፍተኛ ቁጣን አስከትሏል።
የልጅቷ አባት ለፖሊስ ባቀረቡት አቤቱታ አራት ወንዶች ልጅቷን አጎራባች ወደሆነችው ማድያ ፕራዴሽ ግዛት ወስደው ለአራት ቀናት ያህል በቡድን እንደደፈሯት አስረድተዋል። ግለሰቦቹ ወደ መንደሯ መልሰው ካመጧት በኋላ ሸሽተዋል ተብሏል።
በማግስቱ ታዳጊዋ ሪፖርት ለማድረግ ከአክስቷ ጋር ወደ አቅራቢያዋ ፖሊስ ጣቢያ የሄደች ሲሆን በስፍራው የነበረው ፖሊስ እንደደፈራትም ኤንዲቲቪ የዜና ጣቢያ ዘግቧል።
የላሊትፑር ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኒኪል ፓታክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቻይልድ ላይን በተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ወደ ቢሯቸው እንደመጣችና የተፈጠረውን ክስተት በነገረቻቸው ወቅት "ወዲያውኑ ክስ መመስረቱን አረጋግጫለሁ" ብለዋል።
ዜናው በህንዳውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን የፈጠረ ሲሆን በርካቶች ህግና ስርዓትን በተመለከተ ጥያቄ እያነሱ ይገኛል።
የኮንግረስ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሪያንካ ጋንዲ ቫድራ በሂንዲ ቋንቋ ባሰፈሩት የትዊተር መልዕክት "የፖሊስ ጣቢያዎች ለሴቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ ካልሆነ ታዲያ ቅሬታ ለማቅረብ የት ይሄዳሉ?" ሲሉ ጠይቀዋል።
"መንግሥት የሴቶችን ቁጥር በፖሊስ ጣቢያዎች እንዲጨምር፣ የፖሊስ ጣቢያዎች ለሴቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ምን ያህል እያሰበበበት ነው" ሲሉ አክለዋል።
በህንድ ዋና ከተማ ደልሂ አንዲት ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ በቡድን ተደፍራ ህይወቷ ካለፈችበት ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ መደፈር እና ፆታዊ ጥቃቶች ከፍተኛ ትኩረት አግኝተዋል።